ሀረር ህዳር 2/2007 /የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት-ኢዜአ / የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ድርቅና አረምን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 23 የሰብልና የእንሳሳት መኖ ዝርያዎችን እያለመደና እያስፋፋ መሆኑን ገለጸ።
ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ከፊል አርሶ አደር አካባቢ እያከናወነ ያለው የቴክኖሎጂ ሽግግር ትናንት በመስክ ተጎብኝቷል፡፡
የዩኒቨርሲቲው ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ንጉሴ ደቻሳ በጉብኝቱ ወቅት እንደገለጹት እያለመዱና እያስፋፋ ያሉት ምርምር ሲያካሄድባቸው የነበሩና ከሌላ የምርምር ማዕከል የተገኙ የስንዴ ፣ የበቆሎ ፣ የአተር የማሽላ ፣የድንችና የእንስሳት መኖ ዝርያዎች ናቸው፡፡
እነዚህን ዝርያዎች የማላመድና የማስፋፋት ስራ እየተካደ ያለው በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖች በሚገኙ ከፊል አርሶ አደሮች አካባቢ ነው፡፡
በዞኖቹ የሚገኙ 13 የዘር አምራች ማህበራት ማሳና ስድስት የገበሬ ማሰልጠኛ ጣቢያ ላይ ተመራማሪዎችና ከፊል አርሶ አደሮች በጋራ በመሆን ስራውን በጋራ እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።
በማለመድ ወደ አርሶ አደሩ በመስፋፋት ላይ ከሚገኙት መካከል ቀቀባ የተባለው የስንዴና ሜቲ የተሰኘው የአተር ዝርያ የዝናብ እጥረትንና የአረም ወረርሽኝ ሳይበግራቸው በ75 ቀናት ለምርት እንደሚደርስ ዶክተር ንጉሴ ገልጸዋል፡፡
ጉደኔ፣ጃለኔና ቡቡ የተባሉት የድንች ዝርያዎች እንዲሁም የእርግብ አተርና አልፋ አልፋ የተባሉት የእንስሳት መኖ እጽዋቶች ተስማሚና ከብቶችን በአጭር ጊዜ የሚደለቡ በመሆናቸው ወደ አምራቹ እያስፏፏቸው እንደሚገኙ ተናግረዋል።
የቴክኖሎጂው መስፋፋት መንግስት በአርብቶ አደር አካባቢ የሚገኙ የከፊል አርሶ አደሮችን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ የሚያከናውነውን ስራ እንደሚያጠናክረው አመልክተዋል፡፡
በጭናክሰን ወረዳ ሉጉና ዩግ ዩግ ቀበሌ የመስክ ጉብኝቱ ላይ ከነበሩት ከፊል አርሶ አደሮች መካከል አቶ ሐሰን ኢብሳና አቶ ዳውድ በከር ይገኙበታል፡፡
ከፊል አርሶ አደሮቹ እንዳሉት ከዩኒቨርሲቲው ተሻሽለው የሚወጡ የሰብልና ለእንስሳት መኖነት የሚያገለግሉ ምርጥ ዘሮችን ከዘመናዊ የግብርና አሰራሮች ጋር እንዲጠቀሙ አድርጓቸዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የሚጠቀሙባቸው ዝርያዎች የዝናብ እጥረትንና አረምን መቋቋም ስለሚያችሉ ፍሬ ሳይሰጡ እንደሚበላሹባቸው አመልክተው አሁን ግን ምርጥ ዘር በማግኘታቸው የተሻለ ውጤት እያዩ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
በተለይ ቀቀባ፣ሜቲ፣ቡቡ የተባሉት የስንዴ፣የአተርና የድንች ዝርያዎች በፍጥነት የሚደርሱና በሽታ የማያጠቃቸው መሆናቸውን በሰርቶ ማሳያ የሙከራ ስራ መመልከታቸውን ጠቁመዋል፡፡
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር ያወጣቸው ድርቅና በሽታን ተቋቁሞ ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ ከ1260 ኩንታል በላይ የድንችና የስንዴ እንዲሁም 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን የስኳር ድንች ቁርጥራጭ ምርጥ ዝርያዎችን ለምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን አርሶ አደሮች ማሰራጨቱም ተመልከቷል፡፡