ሀረር ህዳር 3/2009 ዓ.ም የሐረማያ ዩኒቨረሲቲ ከሁለት መቶ ሺህ ብር በሚበልጥ ወጪ  የገዛቸውን የማጣቀሻ መጽህፍትና የተለያዩ የጽህፈት መሳሪያዎች ለአዴሌ ማረሚያ ቤት በድጋፍ ሰጠ፡፡

ዩኒቨረሲቲው በአካባቢው እያከናወነ ያለው የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራ በቀጣይም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተገልጿል፡፡

የዩኒቨረሲቲው የማህበረሰብ ልማት አገልግሎትምክትል ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወ/ፃዲቅ ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት እንደገለፁት ዩኒቨረሲቲው ከመማር ማስተማርና ከምርምር ሥራ ጎን ለጎን ለአካባቢው ነዋሪዎችና ለመንግስት ተቋማት የማህበረሰብ አገልግሎቶችን እየሰጠ ይገኛል፡፡

ማረሚያ ቤቱ ለዩኒቨረሲቲው ባቀረበው የፍላጎት ጥያቄ መሰረት 625 የተለያዩ የማጣቀሻ መጽህፍትና የጽህፈት መሳሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨረሲቲው ዕቅድና በጀት በመያዝ በተለያዩ የትምህርት ቁሳቁስ፣በመምህራንና በሌሎች ድጋፉን አጠናክሮ ለመቀጠል ከማረሚያ ቤቱ ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

ድጋፉ የህግ ታሚዎች በማረሚያ ቤት ቆይታቸው በትምህርትና በንባብ ራሳቸውን ለውጠው እንዲወጡ በማድረግ በኩል ጠቀሜታው ከፍተኛ መሆኑን ምክትል ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡

በማረሚያ ቤቱ የታራሚዎች የሥራ ሂደት ኃላፊ ኢንስፔክተር ያህያ አብደላ ድጋፉ በማረሚያ ቤቱ የነበረውን መጽህፍትና የጽህፈት መሳሪያ እጥረት እንደሚያቃልል ነው የገለፁት፡፡

በተለይ በማረሚያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ተማሪዎች በማረሚያ ቤት ውስጥ ያላቸውን ቆይታ በንባብና በመማር እንዲያሳልፉ ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በቀጣይም ዩኒቨረሲቲው የላይብረሪ መፃህፍት፣ኮምፒተሮችና አዲስ ለሚጀመረው የ10ኛ ክፍል ትምህርት በመምህራን ድጋፍ እንደሚያደርግላቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን ኢንስፔክተሩ ተናግረዋል፡፡

አዴሌ ማረሚያ ቤት የሚገኘው ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አስናቀ ምትኬ በበኩላቸው፣ የዩኒቨረሲቲው ድጋፍ በማረሚያ ቤቱ በመማር ማስተማር ሥራ ላይ የሚታየውን ክፍተት ከመሙላት ባለፈ ለተማሪውም ሆነ ለመምህሩ የጎላ ጠቀሜታ እንዳለው ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መምህሩ እንዳሉት መፃህፍቶቹ ለመማር ማስተማር ሥራ አጋዥ ከመሆናቸውም በላይ መምህራኑና ተማሪዎች እንዲያነቧቸው የሚያነሳሱ ናቸው፡፡

“በተለይ ታራሚው የማረሚያ ቤት ቆይታውን በትምህርት ንባብ እንዲያሳልፍ ስለሚየደርጉ ነገ ለሀገሪቱ የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ ያጎለዋል” ብለዋል፡፡

ዩኒቨረሲቲው በቀጣይ በትምህርት ቤቱ ለሚገኙ መምህራን የአቅም ግንባታ ስልጠና እንዲሰጥም ጠይቀዋል፡፡

ከማረሚያ ቤቱ የህግ ታራሚዎች መካከል ወጣት ወንድምአገኘ ተገኝ በበኩሉ መፃህፍቶቹ ለታራሚው የጎላ ጠቀሜታ እንዳላቸው በመግለፅ ዩኒቨረሲቲውን አመስግኗል፡፡

ማረሚያ ቤቱ የሚሰጠው ትምህርት እስከ 9ኛ ክፍል በመሆኑ ተማሪዎች 10ኛ ክፍልን መማር እንዲችሉ ገልፆ፣ዩኒቨረሲቲው ከማረሚያ ቤቱ ጋር በመነጋገር መፍትሄ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡