የትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ 500 ለሚጠጉ ተማሪዎች ስልጠና ሰጠ

በሲሳይ ዋቄ /ሐዩ ኤፍ ኤም 91.5

ተማሪዎች በቡድን ተቀናጅተው የመስራት ችሎታቸውን ለማዳበር የሚያስችል ስልጠናዎችን እየሰጠ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ አስታወቀ፡፡ኮሌጁ በትምህርታቸው የተሻለ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎችም ሰሞኑን ሽልማት ሰጥቷል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅማ ተማሪዎች እርስ በርስ ተጋግዘው መስራት ያለውን ጠቀሜታ ተረድተው ወደ ስራ እንዲገቡ ለማስቻል ሰሞኑን ከ480 በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ የኮሌጁ ተወካይ አቶ ገመቹ አበራ እንደገለፁት ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ደንብ እና መመሪያዎችን አክብረው እርስ በእርስ ተረዳድቶ በቡድን መማርና መስራትን ተግባራዊ ማድረግ ከቻሉ ወደ ስራ ዓለም ሲገቡም ብቁና ተወዳዳሪ ዜጋ ለመሆን የሚያግዳቸው ነገር የለም ብለዋል፡፡

ተማሪዎች ያላቸውን ዕውቀት ለጓደኞቻቸው የሚያካፍሉበትንና እርስ በርስ እያጠኑ ውጤታማ መሆን የሚችሉባቸውን መንገዶች አስመልክቶ ስልጠናውም እንደተዘጋጀ አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

ስልጠናውን ከሰጡት መምህራን መካከል አቶ ፈየራ ዲንሳ እንደገለፁት ተማሪዎች ተመርቀው ወደስራ በሚሰማሩበት ወቅት በሚኖራቸው ብቃት መሰረት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የሚሰጧቸው ትምህርት በመሆኑ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም ብቃት ያላቸውን ዜጎች ለማፍራት እንዲችል በትምህርት አሰጣጡ ላይ በየጊዜው አስፈላጊ ግብኣቶችን በማሟላት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ተመራቂ ተማሪዎች ወደስራ ለመግባት የሚሰጠውን ፈተና ከሚወድቁት ዘጠና ከመቶው የሚሆኑት ከብቃት ማነስ መሆኑ በጥናት መረጋገጡን በስልጠናው ላይ የገለፁት አቶ ዋጋሪ ታሲሳ ይህን ችግር ለማስወገድ የተማሪዎችን ብቃት የማጎልበት ስራ እየተከናወነ መሆኑንና ተማሪዎች በቡድን እንዲያጠኑ የሚደረገውም ተማሪዎች ያለፍራቻ ከአቻዎቻቸው ጋር እርስ በርስ ዕውቀት ቀስመው ብቁ ዜጋ እንዲሆኑ ለማስቻል ነው ብለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የተጀመረው የኮኦፖሬቲቭ ለርኒግ ተማሪዎች እርስ በርስ እየተማማሩ ዕውቀታቸውንና ያላቸውን የትምህርት መርጃ መሳሪያዎችን በጋራ እንዲጠቀሙ ያስችላል ተብሏል፡፡

በትምህርትና ስነ-ባህሪ ኮሌጅ ስር በሚገኙ ትምህርት ክፍሎች ውስጥ ባለፈው ሴሚስተር በትምህርታቸው ከፍተኛ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የማበረታቻ ሽልማት በስልጠናው ማጠቃለያ ወቅት ተሰጥቷቸዋል፡፡