ሀረር /ኢዜአ/ ሃምሌ 2/2008 በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት ወደ ተግባር በማሸጋገር ራሳቸውንና ሀገራቸውን ለመጥቀም ዝግጁ መሆናቸውን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪዎች ገለጹ፡፡
ዩኒቨርሲቲው በተለያየ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን ከ8 ሺ500 በላይ ተማሪዎች ዛሬ አስመርቋል፡፡
ከዕለቱ ተመራቂዎች መካከል በሰላምና ግጭት አፈታት የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ዲግሪ ያገኘው ጀይላን ወልዬ ሁሴን ይገኝበታል፡፡

በትምህርት ቆይታው የቀሰመውን እውቀት ወደ ተግባር በመለወጥ ራሱንና ቤተሰቡን እንዲሁም ሀገሩን ለመጥቀም ጠንክሮ እንደሚሰራ ተናግሯል፡፡
በተለያዩ ምክንያቶች የሚነሱ ግጭቶችን በእውቀት ላይ ተመስርተው እንዲፈቱ ለማስቻል የበኩሉን አስተዋጥኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ገልጿል፡፡
በስጋና ወተት ቴክኖሎጂ በመጀመሪያ ዲግሪ የተመረቀችው ወጣት ሙሉ ጋዲሳ ደግሞ በሰለጠነችበት ሙያ ሀገሯንና ያስተማራትን ህዝብ ለማገልገል ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራላች፡፡
ስራ ጠባቂ ሳትሆን በራሷ ፈጥራ ለመሰማራትም ዝግጁ መሆኗን በሰጠችው አስተያየት ጠቁማለች፡፡
የሲቪል ምህንድስና የማዕረግ ተመራቂው ኢዮስያስ ዳዊት በበኩሉ ባለፉት ዓመታት በግቢው ውስጥ የነበሩትን ፈታኝ ሁኔታዎችን ተቋቁሞ ለዛሬው ምረቃ መድረሱን ተናግራል፡፡
በቆይታው ያገኘውን እውቀት በመጠቀም ስራ ፈጣሪ በመሆን ቤተሰቡንና ሀገሩን ለማገልገል መዘጋጀቱን ገልጿል ፤ መንግስትም ተመራቂ ወጣቶች በሰለጠኑበት ሙያ ወደ ስራ እንዲገቡ በማበረታታት ድጋፍ ማድረግ እንዳለበትም አመልክቷል፡፡
በግብርና ዘርፍ ሰልጥና የተመረቀችው አየሁልሽ ሹምዬ በሰጠችው አስተያየት በዩኒቨርሲቲ ቆይታዋ የቀሰመችውን እውቀት ወደ ተግባር በማሸጋገር ከራሷ አልፎ ሀገሯንም ለመጥቀም በቁርጠኝነት እንደምትሰራ ተናግራለች።
በቆይታዋ ያገኘችውን እውቀት በመጠቀምና ስራ ፈጣሪ ሆና በመንቀሳቀስ የሳይንስና ቴክኖሎጂ እድገትን ለመደገፍ የበኩሏን ጥረት ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የተናገረችው ደግሞ በኤሌትሪካልና ኮምፒተር ምህንድስና የማዕረግ ተመራቂዋ ትግስት አያሌው ናት፡፡
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ እንደተናገሩት በመደበኛ፣ በተከታታይ፣በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ሰልጥነው ከተመረቁት ተማሪዎች መካከል 26ቱ በዶክትሬት ድግሪ፣577 በሁለተኛ ዲግሪና ቀሪዎቹ ደግሞ በመጀመሪያ ዲግሪና ዲፕሎማ ፕሮግራሞች የሰለጠኑ ናቸው፡፡
በዕለቱ ከተመረቁት ተማሪዎች ውስጥ 26 በመቶ ሴቶች መሆናቸውን ያመለከቱት ፕሮፌሰሩ ዩኒቨርሲቲው በ2008 ትምህርት ዘመን የተማሪ ቅበላ አቅሙን ከ33 ሺህ በላይ ማድረሱን አመልክተዋል፡፡

በክብር እንግድነት የተገኙት የእንስሳትና ዓሳ ሀብት ሚኒስትርና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር የቦርድ ሰበሳቢ አቶ ስለሺ ጌታሁን ተመራቂዎቹ ስራ ፈጣሪና ታታሪ በመሆን ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን ማገዝ እንደሚገባቸው ጠቁመው በተለይ ችግር ፈቺ ጥናትና ምርምሮችን በማካሄድ የቀሰሙትን እውቀት ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡