የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች የሚታየውን የጤና ባለሙያ እጥረትና የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ለማቃለል አበረታች ሥራ እየሰራ መሆኑን የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

ዩኒቨርሲቲው ለአራተኛ ጊዜ በጤና ሳይንስ የትምህርት መስክ ያሰለጠናቸውን 137 ተማሪዎች ዛሬ በሕክምና ዶክትሬት ድግሪ አስመርቋል። ከተመራቂዎቹ መካከልም 18ቱ ሴቶች ናቸው።

በምረቃ ሥነስርአቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የሐረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶሙራድ አብዱልሃዲ መንግስት በከፍተኛ ትምህርት ብቃት ያላቸው፣ ሥነምግባር የተላበሱና ኃላፊነት የሚሰማቸው ባለሙያዎችን ለማፍራት ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በአገሪቱ ከፍተኛ የባለሙያ እጥረት ለሚታይበት የጤናው ዘርፍት ኩረት ሰጥቶ መስራቱ በክልሉ፣ አጎራባች ክልሎችና በአገሪቱ የጤና ባለሙዎችን እጥረት በማቃለል ጉልህ ሚና እንዳለው ተናግረዋል።

“በክልሉ ከሚገኙ የጤና ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ እየሰጠ ያለው የሙያ ማሻሻያ ስልጠናም ለሕብረተሰቡ የሚሰጠውን የጤና አገልግሎት በየጊዜው እንዲሻሻል አድርጓል” ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ በጀት መድቦ እያስገነባ የሚገኘው ስፔሻላይዝድ ቲቺንግ ሆስፒታልና የካንሰር ማዕከል ከሐረሪና አጎራባች ክልሎች ወደ አዲስ አበባና ውጭ አገር ለሕክምና የሚሄዱ ዜጎችን ቁጥር ይቀንሳል የሚል እምነት እንዳላቸው ገልጸዋል።

የዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎችም ወደ ሥራ ሲሰማሩ የሙያው ስነምግባር በሚያዘው መሰረት ህብረተሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ ኮሌጁ የአሁኖቹን ተመራቂዎች ጨምሮ ባለፉት ዓመታት 406 ኃኪሞችን አሰልጥኖ ማስመረቁን ገልጸዋል።

በጤናው ዘርፍ የሰለጠነ ባለሙያ ለማፍራትና ለአካባቢው ማህበረሰብ የተሻለ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው በኮሌጁ የማስፋፊያ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው የጤና ትምህርት አሰጣጥና ጥራትን ለማጎልበት በሕይወት ፋና ሆስፒታል በዓይነቱ ልዩ የሆነ ዘመናዊ የማስተማሪያ ሆስፒታልና የካንሰር ሕክምና ማዕከል በአንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እያስገነባ መሆኑን አስታውቀዋል።

እንደ ፕሬዚዳንቱ ገለጻ፣ ማዕከሉ አንድ ሺህ አልጋዎች የሚኖሩት ሲሆን ለአጎራባች ክልሎች ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለመስጠትና ብቃት ያለው የሕክምና ባለሙያ ለማፍራት ዓይነተኛ ሚና ይጫወታል።

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዲኤታ ዶክተር ከበደ ወርቁ በበኩላቸው ለጤና ሕክምና  አገልግሎት ባለሙያው መሰረት መሆኑን ገልጸው፣ የጤና ባለሙያው ብቃቱን፣ እውቀቱን፣ ልምድና ክህሎቱን በየጊዜው ማሳደግ እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።

በዛሬው ዕለት ለምረቃ የበቁ ኃኪሞች በገቡት ቃለ መሀላ መሰረት ወደ ሕብረተሰቡ በሚሄዱበት ወቅት ለሕሙማን ርህራሄ፣ ጥንቃቄና ክብር ያለው አገልግሎት መስጠት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
ከተመራቂዎች መካከል ዶክተር አብረሃም አለማየው አንዳንዴ ዜጎች ተገቢ ሕክምና ሳያገኙ ለሞት እንደሚዳረጉ ገልጾ፣ በቀጣይ በሙያው ያስተማረውን ሕዝብና አገሩን ለማገልገል በቅንነት እንደሚሰራ ተናግሯል።

ተመራቂ ዶክተር ቤተል ጥበቡ በበኩሏ መንግስት የእናቶችንና የሕጻናትን ሞት ለመቀነስ፣ የጤና አገልግሎቱን ለማሻሻልና በሽታን አስቀድሞ ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት ስኬታማ ለማድረግ ጠንክራ እንደምትሰራ ተናግራለች።
በዩኒቨርሲቲው የጤና ሳይንስ ኮሌጁ ዘንድሮ በ11 የቅድመ ምረቃ የስልጠና መስኮች ሁለት ሺህ 785 ተማሪዎች በሕክምና ሳይንስ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ይገኛሉ። ከነዚህ ውስጥ አንድ ሺህ 435ቱ የሕክምና ዶክትሬት ተማሪዎች መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ሐረር /ኢዜአ/ታህሳስ 15/2009