ሐረር ህዳር 3/2007 /የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት-ኢዜአ / በሐረሪ ክልል እየጠፉና እየቀነሱ የሚገኙ የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶችን ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ለመመለስና አዳዲስ የግብርና ቴክለሎጂዎችን ለማስፋፋት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እያከናወነ ያለው ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት የክልሉ ርእሰ መስተዳድር ገለጹ።

ዩኒቨርሲቲው በክልሉ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ለማከናወን የሚያስችለውን ስምምነት ትናንት ከክልሉ መንግስት ጋር ተፈራርሟል፡፡

የሐረሪ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙራድ አብዱልሃዲ ስምምነቱን ከዩኒቨርስቲው ኘሬዚዳንት ጋር ከተፈራረሙ በኋላ እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በክልሉ ለበርካታ ዓመታት በጤና፣ በግብርና፣ በትምህርትና በሌሎች ማህበረሰብ አቀፍ የምርምር ስራዎችን በማካሄድ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በማድረግ ላይ ነው፡፡

ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውናቸው የምርምር ስራዎች ለክልሉ ልማት መፋጠን አስተዋጽኦ ከማድረጉ በላይ በርካታ የክልሉ ነዋሪዎች፣ ተማሪዎችና አርሶ አደሮች የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል፡፡

በክልሉ ኤረር ሸለቆ በተባለው ስፍራ ዩኒቨርሲቲው የሚያከናውነው የምርምር ስራ በግብርናው ዘርፍ የሚስተዋሉ ችግሮችን በመቅረፍ አርሶ አደሩን የዘመናዊ የግብርና ቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እንደሚያደርግ እምነታቸውን ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለይ በክልሉ እየጠፉና እየቀነሱ የሚገኙትን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ቀድሞ ወደ ነበሩበት ለመመለስና ዘመናዊ የግብርና ቴክለሎጂን ለማስፋፋት እያከናወነ የሚገኘውን ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ሐረር የምትታወቅበትን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርት ለመመለስና ለማልማት ከአራት ዓመታት በፊት ከክልሉ መንግስት ሴላት ሚሊኒየም ኢኮሎጂካል ፓርክ ውስጥ 6 ሄክታር መሬት ተረክቦ የተለያዩ ስራዎች አከናውኗል።

ዩኒቨርሲቲው በተረከበው መሬትም የአካባቢው ዝርያ የሆኑ አትክልትና ፍራፍሬን ጨምሮ ለመድሃኒትነት የሚያገለግሉ የተለያዩ ዕጽዋቶች በማልማትና ፓርኩን አረንጓዴ በማድረግ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለክልሉ መንግስት ማስረከቡን አስታውሰዋል።

የአሁኑ ስምምነትም ዩኒቨርስቲው ኤረር ሸለቆ በተባለው ገጠር ቀበሌ 400 ሄክታር መሬት ከክልሉ መንግስት ተረክቦ የተለያዩ የምርምርና ስርጸት እንዲሁም የተሻሻሉ የግብርና ቴክኖሎጂ ስራዎችን በማከናወን አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

በተለይ በምርምር ስራው በክልሉ እየጠፉና እየቀነሱ የሚገኙትን የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች ቀድሞ ወደ ነበረበት ሁኔታ ለመመለስ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ዶክተር ግርማ ተናግረዋል።

በስምምነቱ ላይ የክልሉ የሥራ ኃላፊዎች የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አመራር አካላት የተገኙ ሲሆን በዕለቱም ዩኒቨርሲቲው ባለፉት ዓመታት በአካባቢው የሚገኙትን አርሶ አደሮች የልማቱ ተጠቃሚ ለማድረግ ያከናወናቸው ተግባራት ዙሪያ ገለጻ ተደርጓል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮ የትምህርት ዘመን በእንስሳትና ሰብል ላይ ያተኮሩ 124 የምርምር ፕሮጀክት ቀርጾ እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ መገለጹ ይታወሳል።