የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ  “የላቀ ውጤት ማስመዝገቢያ ዘዴዎች” በሚል ርዕስ ለተቋሙ  መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ስልጠና ሰጠ፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳ እንዳሉት ስልጠናው የሰው ልጅ በኑሮው ውጤታማ መሆን የሚችሉበትን መንገድ ከተለያዩ የአገር ውስጥና የውጭ ተሞክሮዎች በማቆራኘት የሚቀርቡበት በመሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው። “መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሞክሮ በመቅሰም ልምዳቸውን ያጎለብቱበታል ” ብለዋል ።

በተለይ ሰላማዊና ቅን አስተሳሰብ ማዳበር የተቋሙን የመማር ማስተማር ስራና በተማሪዎች መካከል ያሉትን መልካም ግንኙነቶች ወደ ተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚያስችል ጠቅሰዋል።

እንዲሁም የተቋሙ አጠቃላይ የስራ ሂደት ሰላማዊና ውጤታማ እንዲሆን አስተዋጽኦ እንዳለውም ጠቁመዋል።

”የላቀ ውጤት ማስመዝገቢያ ዘዴዎች” በሚል ርዕስ ፅሁፍ ያቀረቡት በኦሮሚያ ክልል በምክትል ፕሬዝዳንት ማዕረግ የኦህዴድ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት ኃላፊ   ዶክተር አብይ አህመድ ምሁራን ከቀለምና ሙያ ትምህርት ጎን ለጎን ሰላማዊና ቀና አስተሳሰብን በማስተማር ለአገር እድገት አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ ዜጎችን የማፍራት ኃላፊነታቸውን መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ምሁራን ለዜጎች የሚሰጡት የቀለም ትምህርትና የሚያከናውኑት የምርምር ስራ የማህበረሰቡን ህይወት ከመቀየር ባለፈ የላቀ የሀገር እድገትና አስተሳሰብ በማምጣት በኩል አስተዋጽኦ እያደረገ ነው ።

ዜጎች ሀገሪቱ ያላትን አንጡራ ሐብትና ባህሎችን  በአግባቡ ተጠቅመው የተሻለ ህይወት እንዲመሩ በማሳወቅ ረገድ ምሁራን ሚናቸውን ሊወጡ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የሰው ልጅ ማህበራዊ በመሆኑ የላቀ አስተሳሰብና እውቀት ቢኖረውም ብቻውን የሚሄድበት ርቀት ውስን ነው፡፡ በመሆኑም በሰላም የመኖር አስተሳሰብ፤በፍቅር የመኖር አስተሳሰብን በማዳበር በጋራ መበልጸግና መስራት እንደሚቻል ነው የተናገሩት፡፡

የስነ አዕምሮ ባለሙያ መምህርና ደራሲ ዶክተር ምህረት ደበበም ሀሳብና ትሩፋት /Idea and Legacy/ በሚል ርዕስ ሳይንሱንና የህይወት ተሞክሯቸውን በማካተት የማነቃቂያ ፅሁፍ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል፡፡

ለሁለት ቀን በቆየው ስልጠና የዋናው ግቢ እንዲሁም ሐረር ከተማ የሚገኘው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች የተሳተፉ ሲሆን መሰል ዝግጅቶች ለወደፊቱም እንዲዘጋጅ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡