ህዳር 10 ቀን 2009 ዓ/ም በዩኒቨርሲቲው የስብሰባ ማዕከል በተደረገው የምክክር መድረክ ላይ የአጎራባች ከተሞች የአስተዳደር ሀላፊዎችና የሐገር ሸማግሌዎች የተገኙ ሲሆን በመድረኩ ላይ  በማህበረሰብልማትስራዎችዳይሬክቶሬትና በሐረማያ ሀይቅ ሁለገብ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ሥር በ2009 ዓ.ምሊሰሩ የታቀዱ  የልማትስራዎች እንዲሁም በአካባቢው የሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ሊሰማሩባቸው በሚችሉ የስራ ዕድሎች ላይ የተደረገ ጥናት ቀርበው በተሰብሳቢዎቹ ውይይት ተድርጎበታል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ኢንተርፕራይዝ ምክትል ፕሬዝዳንት  ፕሮፌሰር ከበደ ወ/ጻዲቅ የተዘጋጀውን ውይይት አስመልክተው እንደተናገሩት  ዩኒቨርሲቲው የሚሰራቸውን ማህበረሰብ አቀፍ ስራዎች በተመለከተ በተለያዩ መድረኮች ከማህበረሰቡ ጋር ዕቅዶቹን አቅርቦ ውይይት በማድረግና በየደረጃው ማህበረሰቡን በማሳተፍ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ገልጸው የዕለቱ ውይይትም በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የዝግጅት ምዕራፍ ላይ ለማካሄድ ታስቦ በተለያዩ ምክንያቶች እስካአሁን ቢዘገይም ዕቅዱን ለመተግበር በሂደት ላይ የምንገኝ በመሆኑ ሊሰሩ በታቀዱ ዕቅዶች ላይ ውይይት ተደርጎ በጋራ ወደ ትግበራ ለመግባትና ስኬታማ ስራ ለመስራት እንዲቻል  የውይይቱ መካሄዱ ትልቅ አስተዋጾ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡

በውይይቱ ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት  ፕሮፌሰር  ጨመዳ ፊኒንሳ እንዳሉት ዩኒቨርሲቲዎች በዋናነት ሶስት ተግባራትን ማለትም የመማር ማስተማር ፣ ጥናትና ምርምር የማካሄድ እንዲሁም  በአካባቢያቸው ለሚገኙ ነዋሪዎች የማህበረሰብ አገልግሎት የመስጠት ተልዕኮዎችን ይዘው እንደተቋቋሙ ገልጸው ከነዚህ ሶስት ስራዎች መካከል ዩኒቨርሲቲዎች የማህበረሰብ አገልግሎት ስራን አቅማቸው በፈቀደ መጠን ያላቸውን የተማረ የሰው ሐይል በማስተባበር እና ማህበረሰቡን በማሳተፍ በጋራ እንደሚያካሂዱት ተናግረዋል ፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ የሚሰራውን ስራ አሳታፊና ውጤታማ ለማድረግ እንዲረዳው ባለፈው ዓመት ማህበረሰቡንና ባለድርሻ አካላትን በማወያየት የማህበረሰብ አገልግሎት ስራ የሚመራበት ፍኖተ ካርታ እንደተዘጋጀና በዚህ ፍኖተ ካርታ ላይም በአካባቢው ያሉ የጎሉ ችግሮችን ለመቅረፍና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶ ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች ተለይተው በቅደም ተከተል እንደተቀመጡ አስታውሰው በየዓመቱ የሚወጡ ዕቅዶችም ይህንን በጥናት የተዘጋጀ ፍኖተ ካርታ መሰረት ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል ፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ብዙውን ጊዜ ከግንዛቤ እጥረት የተነሳ ዩኒቨርሲቲው እንደማንኛውም የመንግስት ተቋም በተመደበለት በጀት እንደሚተዳደር በመዘንጋትና ዩኒቨርሲቲውን እንደ እርዳታ ሰጪ ድርጅት በማየት የተለያዩ ጥያቄዎች ይዘው የመምጣት ሁኔታዎች እናዳሉ ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲው በተመደበለት በጀት መሰረት ዕቅድ አውጥቶ እንደሚሰራ መገንዘብና በዚሁ ዕቅድ ላይ  በጋራ ተወያይቶና አዳብሮ ተቀናጅቶ መስራት እንደሚገባ አመልክተዋል ፡፡

በዕለቱ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ልማትስራዎች ዳይሬክቶሬት በ2009 ዓ.ም ሊሰሩ የታቀዱ የልማት ስራዎችበዝርዝር ቀርበው ውይይት የተደረገባቸው ሲሆን ከነዚህ ሊሰሩ ከታቀዱ ስራዎች መካከልምርትና ምርታማነትን የሚጨምሩና መሰረተ ልማትን የማያስፋፉ ስራዎች እንዲሁም የስራ ፈጠራንና ቢዝነስ ዲቭሎፕመንትን (ኢንተረፕረነርሸፕ) የማገዝ ስራዎች፣ለጤናአገልግሎት መስፋፋት ድጋፍ ማድረግ፣ተፈጥሮንና አከባቢን የመንከባከብ ስራ፣ጥራቱ የተጠበቀ ትምህርት እንዲስፋፋ መስራት፣ለአቅም ግንባታ ትኩረት መሰጠትና ማህበራዊ ፍትህን የማስፋፋት ስራዎች ይገኙበታል ፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ልማት ስራዎች ዳይሬክቶሬትዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አድማሱ ቦጋለ በምክክር መድረኩ የተደረጉ ውይይቶችንና የተሰነዘሩ ገንቢ ሀሳቦችን አስመልክተው እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ ለመስራት ያቀዳቸውን ስራዎች በአሳታፊነት ከማህበረሰቡና ከሚመለከታቸው ቢሮዎች ጋር በቅንጅት ለመተግበር እንዲቻል መድረኩ ትልቅ አቅም የፈጠረ እንደሆነ ገልጸው ዩኒቨርሲቲው እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ የማህበረሰቡን ህይወት ሊያሻሽሉ በሚችሉ የልማት ስረዎች ላይ በትጋት እንደሚሳተፍ ገልጸዋል ፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የተገኙት የሐረማያ ከተማ ከንቲባ አቶ መሀመድ አሊ እንደተናገሩት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ያደገረጉ በርካታ ስራዎች ሲሰራ እንደቆየና በተለይም በግብርናው ዘርፍ በጥናትና ምርምር የተገኙ ምርጥ ዘሮችን ለገበሬው በማከፋፈልና ቴክኖሎጂውን በማስፋፈት ገበሬውን ተጠቃሚ ያደረገ ሰፊ ስራ መስራቱን ብሎም ከግብርናው ባለፈ  በአቅም ግንባታና በስራ ፈጠራ ላይ በርካታ ስራዎችን መስራቱን ገልጸዋል፡፡ አቶ መሀመድ አያይዘው እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው በ2009 ዓ/ም ለመስራት ባቀዳቸው የአቅም ግንባታ፣ የስራ ፈጠራ ፣ የአካባቢ ልማትና ሌሎችም ስራዎች ላይ ውይይት ማድረጋቸውንና የታቀዱት ስራዎችም ለአካባቢው ማህበረሰብ እጅግ አስፈላጊና መሰረታዊ በመሆናቸው ማህበረሰቡን በማስተባበር ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ ለመስራት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

የባቴ ከተማ ነዎሪና የሐገር ሽምግሌ የሆኑት አቶ ጣሀ አብራሂም በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው ወደ ፊት ለማህበረሰቡ የሚሰራውን ስራ በተመለከተ የአካባቢውን ነዋሪ ተወካዮች ጋብዞ ዕቅዱን ማቅረቡ ዩኒቨርሲቲው ምን ለመስራት እንዳቀደ ከማሳወቅ በተጨማሪ ስረዎቹን ተጋግዞ በመስራት ውጤት ለማምጣት እንደሚረዳ ጠቅሰው የታቀዱት ስራዎች ነዋሪውን የሚጠቅሙ በመሆናቸው ዩኒቨርሲቲው ጠንክሮ ስራ ላይ እንዲያውላቸው መልክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአወዳይ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ አብይ ግርማ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአካባቢውን ከተሞች ለማልማትና ማህበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ከአካባቢው ከተሞች ጋር በጋራ እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸው ለአብነትም ዩኒቨርሲቲው ባለፈው ዓመት ለአወዳይ ከተማ የውስጥ መንገድ ስራ የሚውል 1.5 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጎ የኮብል ስቶን መንገድ እንደተሰራና በአሁኑም ወቅት መንገዱ በዩኒቨርሲቲው ስም ተሰይሞ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ የሚሰሩ የልማት ስራዎችን በተመለከተም በዚህ መልኩ በጋራ ውይይት መደረጉ ጠቃሚ እንደሆነም አክለው ተናግረዋል ፡፡