የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለዶክተር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ገምግሞ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ቦርድ ትናንት ታህሳስ 14 ቀን 2012 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ ለዶክተር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱ በእንስሳት ሀብት ልማትና አስተዳደር የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷል፡፡

ዶ/ር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱ ታህሳስ 22 ቀን 1949 ዓ.ም. በሐረር ከተማ በድሮ በሪ (ቡዳ በር) በሚባለው ሰፈር ተወለዱ፡፡ መደበኛ ትምህርት ከመጀመራቸው በፊት የሐረር ቁራን ትምህርት ቤት (ቁራን ጌይ መድረሣ) በመግባት ቅዱስ ቁርዓን ማንበብ (መቅራት) መሠረታዊ የእስልምና ኃይማኖትና ተግባራቶችን የተመለከተ ዕውቀት አገኙ፡፡

በቀጣይም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ሐረማያ ከተማ በመሄድ የመጀመሪያ ትምህርታቸውን በሐረማያ የስዊድን ሚሽን ትምህርት ቤትና በሐረማያ ግብርና ኮሌጅ ተማሪዎች ትምህርት ይሰጥበት በነበረው የባቴ የመለስተኛ ሁለተኛ ት/ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡ የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሐረር መድኃኔዓለም አጠቃላይ 2ኛ ደረጃ በንግድ ሥራ ትምህርት ተከታትለው በማጠናቀቅ በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የሐረማያ ግብርና ኮሌጅ በመግባት በ1973 ዓ.ም. በእንስሳት ሳይንስ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ተመረቁ፡፡
ወደ ሥራ ዓለም ሲቀላቀሉም በአርሲ የገጠር ልማት ማዕከል ውስጥ በእንስሳት ሳይንስ ባለሙያነት ሥራ ጀምረው በማዕከሉ የእንሰሳት ምርምር ክፍል ኃላፊነት ድረስ ደርሰዋል፡፡

በስዊዲሽ አለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (SIDA) የሚደገፈው የአርሲ የገጠር ልማት ማዕከል የተቀናጀ የገጠር ልማትን ስራዎችን ለማካሄድ የተቋቋመ ፕሮጀክት ሲሆን ዶ/ር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱም በፕሮጀክቱ ውስጥ ለሶስት ዓመታት በሰጡት ውጤታማ አገልግሎት ምክንያት በእንስሳት ምግብ አስተዳደር የ2ኛ ዲግሪ የትምህርት ዕድል በስዊድን የግብርና ሳይንስ ዩኒቨርሲቲ አግኝተው ትምህርታቸውን ተከታትለው በ1977 ዓ.ም. ተመርቀዋል፡፡

የሁለተኛ ዲግሪያቸውን እንዳጠናቀቁ ወደ አርሲ የገጠር ልማት ማዕከል በመመለስ በግብርና ልማትና ምርምር ሥራዎች ለ16 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዚህም ጊዜያት የባህላዊ የግብርና አሰራር የአርሶና አርብቶ አደሮች በተሻሻለ የግብርና አሰራር ዘዴዎች ላይ ያለባቸውን የመቀበል ችግርና እንዴት የተሸሻሉ የግብርና አሰራሮችንና የምርምር ግኝቶችን ወደ ተግባር መቀየር እንደሚቻል በቂ ልምድ አግኝተዋል፡፡

በ1989 ዓ.ም. የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የእንሰሳት ሳይንስ ትምህርት ክፍልን በመምህርነት የተቀላቀሉት ዶ/ር መሐመድ ለአምስት ዓመታት ካስተማሩ በኃላ በደቡብ አፍሪካ ፍሪ ስቴት ዩኒቨርሲቲ በመግባት የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በወተት ልማት በ2003 ዓ.ም. ጨርሰው ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰዋል፡፡

ዶ/ር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ፣የምርምር ሥራዎችና የማህበረሰብ አገልግሎት ሥራዎችን በማከናወን ለ22 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተለያዩ ምርምሮችን በማካሄድ፣ የተለያዩ ፕሮጀክቶችን በማዘጋጀትና በመተግበር ፣ ሥልጠናዎችንና የምክር አገልግሎቶችን በመስጠት ለግብርናው ዘርፍ ዕድገት የበኩላቸውን ከፍተኛ ኃላፊነት በሚገባ ተወጥተዋል፡፡ ባለሙያዎች ከማፍራት አንፃር ለ66 የማስተርስ ዲግሪና ለዘጠኝ የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች ዋናና ረዳት አማካሪ በመሆን በሰው ኃብት ልማቱም አስተዋፅዖ አበርክተዋል፡፡ በሀገርና ዓለም አቀፍ ደረጃ የድህረ ምረቃ ተማሪዎች ፈታኝ በመሆንም አገልግለዋል፡፡

ዶ/ር መሐመድ 97 የምርምር ሥራዎችን በዋናና በረዳት ፀሀፊነት፣ 67 የምርምር ፅሁፎችን ፣ 12 የምርምር ፅሁፍ የያዙ መፅሐፎችንና 18 ልማትን የተመለከቱ ሪፖርቶችን አዘጋጅተው ለህትመት አብቅተዋል፡፡ በምርምር ህትመት ሥራዎቻቸውም የግመል ፣ የጋማ ከብቶችን ፣ የቀንድ ከብቶችንና የዶሮ እርባታ ዘዴዎችን የተመለከቱ የምርምር ፅሁፎችን አሳትመዋል፡፡

ከማስተማርና የምርምር ሥራቸው ባሻገር በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ በተለያዩ ኮሚቴዎችና ፕሮጀክቶች ውስጥ በኃላፊነት ቦታዎች ላይ አገልግለዋል፡፡ በተመሳሳይም በሀገርና አህጉር አቀፍ የሙያ ማህበሮችም ውስጥ በተለያዩ ደረጃዎች አገልግለዋል፡፡
በተለያዩ የትምህርትና የምርምር ሥራዎች ውስጥ ያላቸውን ዕውቀት ለሌሎች በማካፈልና የተሸለ ውጤት ማግኘት የሚቻልባቸውን መንገዶች ከሥራ ባልደረቦቻቸው ጋር በማፈላለግ ላከናወኑት ከፍተኛ አስተዋፅዖ በተለያዩ ጊዜያት ካገኟቸው ሽልማቶች በተጨማሪ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የረዳት እና የተባባሪ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ በተለያዩ ጊዜያት ተሰጥቷቸዋል፡፡

ዶ/ር መሐመድ ዩሱፍ ኩርቱ ለፕሮፌሰርነት ማዕረግ እንድበቃ የበኩላቸውን ከፍተኛ ዕገዛና ድጋፍ ላደረጉልኝ ቤተሰቦቼ ፣ የሥራ ባደረቦቼ ፣ ተማሪዎቼና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አመራሮች ከፍተኛ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ብለዋል፡፡