ኢዜአ/ሐረር /ሀምሌ 8/2006

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ግምታቸው ከሁለት ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ የማጣቀሻ መጽሐፍትና ኮምፒተሮችን ለአካባቢው ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በእርዳታ ሰጠ።

የትምህርት ቁሳቁሱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚከናወነውን ስራ ይበልጥ የሚያጎለብት መሆኑን የትምህርት ባለሞያዎች ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዜዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ የትምህርት ቁሳቁሶቹን ካስረከቡ በኋላ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማርና ምርምር ስራ ጎን ለጎን በማህበረሰብ አገልግሎት ለበርካታ ዓመታት የተለያየ ስራ እያከናወነ ይገኛል።
ለትምህርት ቤቶቹ የሰጠው ቁሳቁስ በአሜሪካን ሚኔሶታ ግዛት የሚኖሩ የምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ ቡክ ፎር አፍሪካ ከሚባል ተራድኦ ድርጅትና ከፈቃደኛ ግለሰቦች ጋር ስምምነት በመፈራረም የተላከለትን 22 ሺህ የማጣቀሻ መጽሃፍትና 34 ኮምፒተሮች መሆናቸውን ተናግረዋል።

የኒቨርሲቲው በመጀመርያ ዙር ከለጋሾች ያገኛቸውን የማጣቀሻ መዕሃፍትን ኮምፒተሮችን በሐረሪ ክልል፣በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ለ20 ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ማከፋፈሉንም ገልጸዋል።

መጽሃፍቶቹና ኮምፒውተሮቹ በተለይ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የሚታየውን የመርጃ መጽሀፍት እጥረትና የኮምፒተር አጠቃቀም ችግር በተወሰነ መልኩ እንደሚያስወግድ ገልጸዋል።

ከድጋፍ አድራጊዎቹ ያገኛቸው ተመሳሳይ መጽሃፍትና ኮምፒተሮችን ጨምሮ ማይስክሮኮፖችና የላቦራቶሪ እቃዎች ከጅቡቲ ወደብ በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኙ ዶክተር ግርማ ገልጸዋል።

የማጣቀሻ መጽሃፍትና ኮምፒተሮችን ከተረከቡት መካከል የሐረማያ ወረዳ ፣የሐረሪ ክልልና የምዕራብ ሐረርጌ ትምህርት ቢሮ ተወካዮች አቶ ይስሃቅ ዳውድ፣አቶ ፈቲ አብዱላሂና አህሳን መሐመድ እንደተናገሩት የትምህርት ቁሳቁሱ የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የተጀመረውን ስራ ይበልጥ የሚያጎለብት ነው።

በተለይ በአሁኑ ሰዓት በትምህርት ቤቶች ውስጥ የላቦራቶሪና የኬሚካል እጥረት እንዳለባቸው ጠቁመው ይህን ችግር ዩኒቨርሲቲው እንዲያስወግድላቸው ጠይቀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ90 ሚሊየን ብር የሚበልጥ ግምት ያላቸው የህክምና ቁሳቁሶች በአካባቢው ለሚገኙ አምስት ሆስፒታሎች መስጠቱ ይታሳል።