የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህግ ኮሌጅ በሰብአዊ መብት፣ በወንጀል ህግ እና በታራሚዎች አያያዝና መብት ዙሪያ ከሐረሪ ክልል፤ እና በኦሮሚያ ክልል ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ማረሚያ ቤቶች ለተውጣጡ ስልሳ ባለሞያዎች ለሶስት ቀናት የቆየ ስልጠና ሰጠ፡፡

በስልጠናው መክፈቻ ላይ ንግግር ያደረጉት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተሳትፎና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕ/ር ከበደ ወ/ጻዲቅ እንደተናገሩት መድረኩ ሰልጣኞች በፖሊሳዊ ስልጠና ያገኙትን ዕውቀት ለማጎልበት እንዲረዳና በተግባር ስራ ላይ በሚያጋጥሟቸው የህግ ክፍተቶች ላይ ልምድ ካላቸው የህግ መምህራን ጋር ተወያይተው የጋራ ግንዛቤ ለመጨበጥ እንዲችሉ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የስልጠናው አስተባባሪ እና በህግ ኮሌጅ መምህር የሆኑት አቶ መንገሻ ወሰን እንደገለጹት የህግ ኮሌጅ በማህበረስብ ተሳትፎ ዘርፍ የፍትህ ተደራሽነትንና የህግ ንቃትን ለማሳደግ በስፋት እየሰራ እንደሆነና ለአብነትም በኦሮሚያ ክልል በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ እንዲሁም በሐረሪ ክልል ውስጥ አርባ አንድ ቢሮዎችን በመክፈት ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎትና የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት እየሰጠ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውሰውል ፡፡

አያይዘውም ስልጠናው የዚሁ የህግ ግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አንድ ክፍል እንደሆነና በማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ውስጥ ለሚሰሩ ፖሊሶች በዋናነት በሰበአዊ መብት ምንነትና አከባበር ፣ በወንጀል ህግ ዓላማና ይዘት እንዲሁም በታራሚዎች መብትና በፖሊሶች ኃላፊነት ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ታስቦ ከዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ ተሳትፎ ምክትል ፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ጋር በመተባበር እንደተዘጋጀ ተናግረዋል፡፡

ተሳታፊዎች በህግ መምህራኑ የሚሰጣቸውን ስልጠና በመከታተል ፣ የቡድን ውይይት በማድረግና በስራ ላይ ያጋጠሟቸውን ችግሮች አንስተው በመወያየት የነቃ ተሳትፎ አድርገዋል፡፡

በስልጠናው ላይ ተሳታፊ የሆኑት የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ማረሚያ ቤት ኃላፊ ም/ል ኢ/ር መገርሳ ወርቁ ስልጠናውን አስመልክተው እንደተናገሩት የተሰጠው ስልጠና አባላት ባላቸው መጠነኛ ግንዛቤ አማካኝነት የሚፈጠሩ የአሰራር ክፍተቶችን ለመዝጋት የሚያስችል እንደሆነ ገልጸዋል ፡፡ አክለውም ዩኒቨርሲቲው በሁለቱም ወገን በማረሚያ ቤቶች ውስጥ ቢሮዎችን ከፍቶ ለታራሚዎች ነጻ የህግ ድጋፍ አገልግሎትና የህግ ትምህርት በመስጠት እንዲሁም ፖሊሶችን በማሰልጠን እያደረገ ያለው ድጋፍ ሰብአዊ መብት እንዲከበርና የህግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል፡፡

ከሐረሪ ክልል ማረሚያ ቤት ኮሚሽን የመጡት ም/ል ኮ/ር ሐይሉ በቀለ በበኩላቸው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ ማረሚያ ቤት ጋር በመሆን ለታራሚዎች መብትና ግዴታቸውን በማስተማር እና ጉዳያቸውን የመከታተል አገልግሎት በመስጠት በጋራ እየሰራ እንደሆነ አስታውስው አሁን ደግሞ ለማረሚያ ቤቱ የፖሊስ አባላት የሰጠው ስልጠና ያለውን የአቅም ውስንነት ለመቅረፍ ትልቅ ድርሻ ስላለው በህግ ዙሪያ የሚሰጣቸውን ስልጠናዎች አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የህግ ኮሌጁ ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በዚህ ስልጠና ተሳታፊ ላልነበሩ የማረሚያ ቤት ፖሊሶች በቀጣይ ዙር ለመስጠት ዕቅድ እንደተያዘ ከመድረኩ ተገልጿል ፡፡