በሸምሰዲን መሀመድ የህዝብና ዓለም አቀፍ ዳይሬክቶሬት
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት አራተኛ ዓመት በዓልን አስመልክቶ መጋቢት 26 ቀን 2007 ዓ.ም በዋና ግቢ በነባሩ ስቴዲዮም ላይ በተካሄደው የስፖርትና የመዝናኛ ፕሮግራም ላይ የግድቡ ግንባታ እስኪጠናቀቅ የዩኒቭርሲቲው ማህበረሰብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ጥሪ ቀርቧል፡፡
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ግርማ አመንቴ በዝግጅቱ ላይ ባደረጉት የመክፈቻ ንግግራቸው ሀገራችን እያስመዘገበች ያለችውን የልማትና የዕድገት ግስጋሴ አውስተው ለዚህም የበቃነው በህዝባችን ያላሰለሰ ትግል ውጤት መሆኑን አውቀን ለቀጣይ ድሎችም ሁላችንም በበለጠ እጅ ለእጅ በመያያዝ ዋንኛ ጠላታችን በሆነው ድህነት ላይ ልንረባረብ ይገባናል ብለዋል፡፡
ዶ/ር ግርማ በማያያዝም መንግስት ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መስፋፋት በሰጠው ትኩረት ካለፉት ጥቂት አመታት ወዲህ በዩኒቨርሲቲያችን ትልልቅ ፕሮጀክቶችን በመገንባት የትምህርት ጥራትን በማስጠበቅ ወጣቶች በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ የነበረባቸውን ችግር በተጨባጭ እየፈታላቸው መሆኑን አመልክተዋል፡፡

‘የዚህ የስፖርትና የመዝናኛ ፕሮግራም አላማው አሻናፊና ተሸናፊ ለመለየት ሳይሆን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ያለንን ድጋፍ የምንገልፅበት አንዱ መድረክ ነው” ሲሉ ዶ/ር ግርማ ተናግሯል ። እስከ አሁን ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ድጋፋቸውን ላደረጉ በሶስቱም ካምፓስ የሚገኙትን መምህራን፤ሰራተኞችንና ተማሪዎችን አመስግነው የግድቡ ግንባታ ፍፃሜ እውን እስኪሆን ድረስ እየተደረገ ያለው ዘርፈ ብዙ ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ አቅርበው ያጋመስነውን ግንባታ እንጨርሳለን ብለዋል፡፡


የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ህብረት ፕሬዝዳንት ተማሪ አብዱረዛቅ ከዲር እንደተናገረው የመላው የሀገራችን ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች አሻራ ያረፈበት ታላቁ የህዳሴ ግድባችን እስኪጠናቀቅ ድረስ ሌሎች እንዳደረጉት ሁሉ እኛም ተማሪዎችም የበኩላችንን ለማበርከት ከወር ቀለባችን በመቀነስ ድጋፋችንን አጠናክረን እንገፋበታለን ብሏል፡፡
በአሁኑ ወቅት የዩኒቨርው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቁጥር ከአምስት ሺህ በላይ የደረሰ ሲሆን በሁለተኛው ዙር የቦንድ ግዥ ከጥር ወር 2007 ዓ.ም ጀምሮ ከ13 ሚሊዮን ብር የሚበልጥ የቦንድ ግዥ እንደሚፈጽሙ ለማወቅ ተችላል።

በመጨረሻም በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የውስጥና የውጪ ስፖርት ውድድሮች ደይሬክቶሬት አዘጋጅነት በዩኒቨርሲቲው ጤና ቡድንና በተማሪዎች ቡድን መካከል በተካሄደው የእግር ኳስ ውድድር የተማሪዎች ቡድን የዩኒቨርሲቲውን የጤና ቡድን 1 ለ 0 በሆነ በማሸነፍ የዋንጫ ባለቤት በመሆን ከእለቱ የክብር እንግዳ ከሆኑት ዶ/ር ግርማ አመንቴ እጅ ዋንጫና የቦንድ ሽልማት የተቀበሉ ሲሆን በፓራ ኦሎምፒክ ወንዶች ሩጫ ውድድር ከ1ኛ-3ኛ የወጡት አሸናፊዎችም በተመሳሳይ ሁኔታ የተዘጋጀለቸውን የቦንድ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡