በህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለ34 ዓመታት በመምህርነትና በተመራማሪነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር ሕሉፍ ገ/ኪዳን ባደረባቸው ድንገተኛ ሕመም በተወለዱ በ55 ዓመታቸው ሰኔ 19 ቀን 2006 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሕሉፍ ከአባታቸው አቶ ገ/ኪዳን ተድላ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በላይነሽ ረዳ ሚያዚያ 4 ቀን 1950 ዓ.ም በትግራይ ክልል አደዋ ከተማ ተወለዱ፡፡ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአድዋ ከተማ የተከታተሉ ሲሆን የከፍተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለማያ ግብርና ኮሌጅ ከ1970-72 ተከታትለው በዕፀዋት ሳይንስ በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

ከዚያም በቀድሞው አለማያ ግብርና ኮሌጅ በ1973 በረዳት ምሩቅነት ተቀጥረው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኃላ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በዚሁ ኮሌጅ ተከታትለው በ1977 ዓ.ም በአግሮኖሚ (Soil Science) ተመርቀዋል፡፡ በመቀጠልም በአሜሪካን በአሪዞና ዩኒቨርሲቲ በሶይል ኤንድ ወተር ሳይንስ (Arid Land Resource Science) በ1987 ዓ.ም በዶክትሬት ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡
ከሙያቸው ጋር በተያያዙ ከ15 በላይ በተለያዩ ሀገራት አጫጭር ስልጠናዎችን ወስደዋል፡፡ ከ60 በላይ ሀገር ዓቀፍና ዓለም ዓቀፍ ወርክሾፖች ላይ ተሳትፈዋል፡፡ፕሮፌሰር ሕሉፍ ከ75 በላይ የኤም ኤስ ሲና ከ20 በላይ የፒኤችዲ ተማሪዎችን አማክረው አስመርቀዋል፡፡ በተለያዩ የአካዳሚክና የምርምር የሃላፊነት ቦታዎች ላይ ሰርተዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሕሉፍ ከ50 በላይ ሳይንሳዊ የምርምር ፅሑፎችን በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታዋቂነትን ባተረፉ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ በተጨማሪም ከ17 በላይ ጥናታዊ ፅሑፎችንና በርካታ የማማከር ስራዎችን (አገልግሎቶችን) አከናውነዋል፡፡
ፕሮፌሰር ሕሉፍ የበርካታ የሙያ ማህበራትና በቅርቡ የተመሰረተው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ አባል ነበሩ፡፡
ፕሮፌሰር ሕሉፍ ከሰኔ 2000 ዓ.ም ጀምሮ ላበረከቱት የመማር ማስተማር፣ የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረጋቸውን አግኝተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ በሙያቸው ለሀገራቸውና ለሕዝባቸው እንዲሁም ለዓለም ዓቀፍ ሳይንስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ትጉህና ታታሪ ምሁር ነበሩ፡፡
የቀብር ስነ- ስርዓታቸው ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት በሐረር ስላሴ ቤተ- ክርስቲያን ይከናወናል፡፡
ፕሮፌሰር ሕሉፍ ባለትዳር እንዲሁም የአንድ ሴትና የአንድ ወንድ ልጆች አባት ነበሩ፡፡
የዩኒቨርሲቲው አስተዳደርና ሰራተኞች በፕሮፌሰር ሕሉፍ ገ/ኪዳን ሕልፈተ ህይወት የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን እየገለፁ ለቤተሰቦቻቸው እንዲሁም ለወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛሉ፡፡