ሰላምና ግጭትን በመረዳት ግጭትን መፍታት ለዘላቂ ልማት ያለው አስተዋጾ በሚል ርዕስ ከተለያዩ ክፍሎች ለተወጣጡ የጸጥታ አባላት ለሶስት ቀናት ከ8-10/4/2008 ዓ/ም የቆየ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ልማት ዳይሬክቶሬት ከሶሺዎሎጂ ትምህርት ክፍል ጋር በመተባበር በተዘጋጀው ስልጠና ላይ 25 ሰልጣኞች ከኦሮሚያ አድማ በታኝ ፖሊስ ፣ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጥበቃና ከተማሪዎች የሰላም ፎረም ክለብ አባላት ተሳታፊ ሆነውበታል፡፡

ስልጠናው በዋነኛነት የግጭት መንስኤዎች ምንድናቸው? ግጭቶች በአግባቡና በተገቢው ጊዜ ካልተፈቱስ የሚያስከትሉት ጉዳት ምንድነው? ግጭት መፍቻ ባህላዊ መንገዶች ምን ይመስላሉ?  ሰላምና ልማት ያላቸው ግንኙነትና ቀጣይነት ያለው ሰላም እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል በሚሉ ጉዳዮች ላይ አተኩሮ የቀረበ ነው፡፡

የስልጠናው ተሳታፊ የሆኑት ሳጅን ሙሉሰው ስሜ እንደገለጹት ከስልጠናው ስለ ሰላም ፣ ሰለ ግጭት መንስኤዎች እና ስለ እድገት ሰፊ ትምህርት እንዳገኙና በተለይም ግጭት እንዴት እንደሚፈጠር ከተፈጠረ በኋላም እንዴት መፈታት እንዳለበት እና ሰላም ለዘላቂ የሐገር እድገት ያለውን አስተዋጾ በተመለከተ ትምህርት እንዳገኙ ጠቅሰው ከስልጠናው ያገኙት ዕውቀት ለሌሎች አባሎቻቸውም ለማካፈልና ለማስተማር ማሰባቸውን ተናግረዋል፡፡

በሶሺዎሎጂ ዲፓርትመንት ዲን የሆኑት መምህር ደሜ ዲሪባ በበኩላቸው እንደተናገሩት ስልጠናው በዚህ እርዕስ ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ እንደተሰጠና በቀጣይም ያገር ሽማግሌዎችንና የሐይማኖት አባቶችን በማሳተፍ ለመስጠት እንደታቀደ ገልጸዋል፡፡