በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ ሒደት እንዲጠናከር በቅንጅት እንሰራለን ሲሉ የሐይማኖት አባቶችና የአገር ሽማግሌዎች ተናገሩ።
ዩኒቨርሲቲው ከአካባቢው ማህበረሰብ ፣ ከአገር ሽማግሌዎችና ከሐይማኖት አባቶች ፣ አባገዳዎችና ወጣቶች ፣ ከአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ጋር በሰላማዊ መማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ ውይይት አካሂዷል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በ62 ዓመት የመማር ማስተማር ታሪክ ከ90ሺ በላይ ተማሪዎችን ከዲፕሎማ እስክ ዶክትሬት ድግሪ ያስመረቀ ሲሆን ዘንድሮም የመማር ማስተማሩን ሂደት ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለማከናወን በዝግጅት ላይ ነው።
ዩኒቨርሲቲው ባዘጋጀው ውይይት ላይ የተገኙት የአካባቢው ማህበረሰብ፣ የሀይማኖት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች እንደተናገሩት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሒደት እንዲጠናከር በቅንጅት እንሰራለን፤ ተቋሙም በሁሉም ዘርፎች ላይ የሚያከናውነውን የክትትልና ቁጥጥር ስራን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
ከአካባቢው የአገር ሽማግሌ አቶ ሲራጅ አህመድ የመማር ስራ ለመንግስት ብቻ የሚተው አይደለም፤ የሁሉንም አካላት ርብርብ ይፈልጋል፤ በይበልጥ ደግሞ የአገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶችን ጥረት ይጠይቃል።
የተጣለብንን ሐላፊነት ከተቋሙ ጋር በጋራ በመሆን የመምከር የመገሰጽ እንዲሁም ደግሞ ተማሪዎች ትምህርታቸውን በሙሉ ልብ መከታተል እንደሚገባቸውና በተለያዩ አካላትና ማህበራዊ ድረ ገጽ የሚናፈሱ መረጃዎችን በተገቢው መንገድ መፈተሽ እንደሚገባቸው የማስተማር ሐላፊነታችንን እንወጣለን።
በተቋሙ ባለፉት ዓመታት የመማር ማስተማር እንቅፋት ሲፈጠር ችግሮችን በጋራ እየፈታን ቆይተናል ያሉት አባገዳ ሙሳ ሮባ ዘንድሮ የለውጡ አካል የሆኑትና ወደ ተቋሙ የሚመጡ ልጆችን በሰላም ትምህርታቸውን እንዲከታተሉ የተቻለንን እንሰራለን።
ተቋሙም ከገዢውም ሆነ ከየትኛውም የተፎካካሪ የፖለቲካ ድርጅት አመለካከት የነጻ የመማር ማስተማሪያ ስፍራ እንዲሆን ፤ እንዲሁም በተቋሙ አካባቢ አደንዛዥ እጾች ላይ የቁጥጥር ስራ ማከናወን ይገባል ሲሉ መላከ ስብሐት ውለታው ሞላ ተናግረዋል።
መላከ ስብሐት ውለታው ሞላ ተማሪው የሀይማኖት አባትን ስለሚሰማና ስለሚያከብር ወደ እምነት ተቋም ሲመጡ የሀይማኖት አባቶች ስለመቻቻል እና አብሮ መኖር ከምንም በላይ ማስተማር ይገባናል፤ በየእምነት ተቋሙ ያሉት የሀይማኖት አባቶች ትስስራቸውን ማጠናከርና በሰላም ላይ ልንሰራ ይገባል።
በተቋሙ በተማሪዎች መካከል ችግር ሲከሰት ተማሪዎች ወደ እኛ ነው የሚመጡት ከተቋሙም ጋር ተነጋግረን የማስታረቅ ስራ እናከናውናለን በዚህም አንድም የትምህርት ሰዓት እንዳይባክን እናደርጋለን ያለችው የአካባቢው ነዋሪ ሳፍያ ዩስፍ በተለይ በአሁኑ ወቅት ወደ ተቀሙ የሚመጡ ሁሉንም ተማሪዎችን ለመቀበል በዝግጅት ላይ እንገኛለን ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ “ማህበረሰቡ ፣ የአገር ሽማግሌዎችና የሐይማኖት አባቶች ፣ አባገዳዎችና ወጣቶች በሰላማዊ መማር ማስተማር ላይ ከተቋሙ ጋር ሁሌም እየሰሩ ይገኛሉ”
ዘንድሮም ለውጡን የማይፈልጉ አካላት በተማሪዎች ላይ ሁከት ለመፍጠር ስለሚችሉ ከተቋሙ ጋር ያላቸውን ትስስር በማጠናከር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራውን ማጎልበት አለባቸው፤ የአካባቢው ወጣቶችን ተማሪዎችንም የማስተማርና የመምከር ስራን ማዳበር ይገባል።
ተሳታፊዎቹ መማር ማስተማሩ ስራ ላይ እንቅፋት ሊሆኑ ይችላሉ ብለው ያነሷቸውን አስተያየቶች ተቋሙ በትኩረት እንደሚሰራበት ተናግረዋል።

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዚደንት ፕሮፌሰር ጀይላን ወልዪ ተማሪዎች የተለያዩ ባህሎች፣ ሐይማኖቶችና ቋንቋዎች ያሏቸው ብቻ ሳይሆን ከተለያየ አካባቢ የሚመጡ በመሆናቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ይህንን ተገንዝቦ በቤተሰባዊነት መንፈስና በሠላማዊ መንገድ ተቀብሎ፣ ችግሮችን በመወያየት እየፈታ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በጋራ እየተመካከረ መስራት እንዳለበት ገልፀዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ አያይዘውም አንዳንድ የራሳቸውን የግልና የቡድን ፍላጎት ከአገርና ከህዝብ ፍላጎትና ጥቅም በላይ ለማስጠበቅ የሚንቀሳቀሱ የአገርን ሠላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንዳሉ ማህበረሰቡ ተገንዝቦ በመከላከል የህግ የበላይነትን ማስከበር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡
በተመሳሳይ መድረኮች ከዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ጋር በተካሄደው ውይይት ለመማር ማስተማር ሂደቱ መሰናክል ሊፈጥሩ የሚችሉ ጉዳዮች ለይተው በማውጣት የእርምት ስራ ማከናወን መጀመራቸውን ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲውን የፀጥታ ማስጠበቅ ስራ ላይ የሚሳተፉ አካላት ባደረጉት ውይይትም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲኖር የሚያከናውኑትን ስራ ከዚህ ቀደም ከነበረው አሰራር በተለየ በአንድ አቋም በቅንጅት ለመስራት ዝግጅታቸውን ማጠናቀቃቸውን ጠቁመው ይህም ቀደም ባሉት ጊዜያት ግጭት ሲፈጠር የሚያጋጥሙ የአሰራር ክፍተቶችን እንደሚያስቀር ተናግረዋል፡፡