የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ የልደት፣የጋብቻ፣የፍቺና የሞት ምዘገባዎች የሚካሄዱበት አሰራር ሲሆን በቅርቡ በአገር አቀፍ ደረጃ ምዘገባው በይፋ ተጀምሮ ወደ ስራ መገባቱ ይታወቀል፡፡
ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ተኮር ልማት ዳይሬክቶሬት ከሐረማያ ወረዳ የወሳኝ ኩነት ምዝገባ ኤጀንሲ ጋር በመሆን ከ34 ቀበሌዎች ለመጡ የጤና ባለሞያዎች ፣ የቀበሌ ሊቀመንበርና የአስተዳደር ሰራተኞች ሐምሌ 22/2008 ዓ/ም በሐረማያ ከተማ በወሳኝ ኩነት መሰረታዊ ጽንሰ ሃሳብና አተገባበር ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ሰጥቷል ፡፡

የሐረማያ ወረዳ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ሐላፊ ወ/ሮ ረውዳ አብዶ በበኩላቸው በስልጠናው ላይ የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በማንና እንዴት መከናውን እንዳለበት እንዲሁም መረጃዎች ወጥ በሆነ መልኩ ተይዘው መቀመጣቸው ያለው ጠቀሜታ እንደተብራራ ገልጸው ከዚህ በፊት የእናቶችና ህጻናት ሞትን ለመቀነስ የሚሰሩ ስራዎች የሚታቀዱትም ሆነ የሚመዘኑት በቁንፅል መረጃ ላይ ተመስርተው በመሆኑ የተፈለገውን ውጤት ለማምጣት የተሟላ መረጃ እጥረት አሉታዊ ተፅዕኖ እንደነበረው አስታውሰዋል፡፡
የወረዳው የወሳኝ ኩነቶች ኤጀንሲ ሐላፊ የሆኑት አ/ቶ አብዲ መሐመድ ኑር እንደተናገሩት ምዝገባው ቀደም ብሎ መጀመር የነበረበት ቢሆንም በተለያዩ ምክንያቶች እንደዘገየና አሁን ባለሞያዎቹ በስልጠናው ላይ ስለ ኩነት ምዝገባው ግንዛቤ ከያዙ በኃላ በቀጥታ ወደ ስራ እንደሚገባ ጠቅሰው ከዚህ ቀደም የወሳኝ ኩነቶች ምዝገባ በተበታተነ መልኩ ይካሄድ እንደነበረና አሁን ምዝገባው ተጀምሮ ወደ ስራ ሲገባ ይህን አሰራር በማስቀረት የተሟላ መረጃ ለመያዝ እነደሚያስችል ገልጸዋል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአቅም ግንባታ ስልጠና ሲሰጥ እንደነበር የገለጹት አ/ቶ አብዲ ፥አሁንም ዩኒቨርሲቲው እንደተለመደው ከጎናቸው በመሆን ስልጠናውን የሚሰጥ ባለሞያ በመመደብና ወጪዎችን በመሸፈን ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
የአካባቢው ማህበረሰብ ለመመዝገብ የሚያስፈልጉ መረጃዎችን አሟልቶ በመቅረብና በመመዝገብ ለስራው ስኬታማነት የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠይቋል ፡፡