ኢትዮጵያ ለወተት ከብት እርባታ ምቹ የሆነ የአየር ንብረት ቢኖራትም በወተት ምርት እርባታ ግን ዝቅተኛ ከሚባሉ ሀገራት ተርታ ትገኛለች፡፡ ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያትም የተመጣጠነ የመኖ አቅርቦት አለመኖር ፣ ሳይንሳዊ የሆነ የወተት ከብት አያያዝ እና የወተት አመራረት ዘዴዎችን በትክክል አለመከተል ናቸው፡፡ በመሆኑም የወተት ከብት አርቢዎች በሳይንሳዊ መንገድ በመታገዝ እንዲሰሩ ይጠበቃል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ ልማት ስራዎች ዳይሬክቶሬት ከግብርናና ከአካባቢ ሳይንስ ት/ት ክፍል ጋር በመሆን ከሐረር ፣ ከአወዳይ ፣ ከሐረማያ እና ድሬዳዋ ከተሞች ለመጡ 80 በወተት እርባታ ስራ ላይ ለተሰማሩ ሰዎች ከታህሳስ 22 እሰከ 23/2009 ዓ.ም የተግባር ስልጠና ሰጥተዋል፡፡

የተግባር ስልጠናው በዋነኛነት በወተት ከብት መኖ አዘገጃጀት ፣ በወተት ከብቶች አያያዝ ፣ በወተት ከብት አረባብና በሰው ሰራሽ ማዳቀል ዘዴ ላይ በማተኮር የተሰጠ ሲሆን በተጨማሪም ሰልጣኞች የዩኒቨርሲቲውን የወተት ከብት እርባታ ጣቢያ በመጎብኘት በከብቶች የጤና አጠባበቅና አጠቅላላ አያያዝ ላይ ልምድ እዲቀስሙ ተደርጓል፡፡
የመርሐ ግብሩ አንድ ክፍል በሆነው የምክክር መድረክ ላይም የዩኒቨርሲቲው ሐላፊዎችና ባለሞያዎች በተገኙበት ዘርፉን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማደረስ በቀጣይ በጋራ መሰራት ባለባቸው ጉዳዮች ላይ እንዲሁም ሰልጣኞች በነሷቸው ነጥቦች ላይ ሰፊ ምክክር ተደርጓል፡፡
“በሁለት ቀን ውስጥ ካገኘነው እውቀት አንጻር ዩኒቨርሲቲው ይህንን ስልጠና ለመስጠት ዘግይቶል ቢሆንም ግን ወደፊት ተቀራርቦ መስራት ይገባል ” ያሉት ሰልጣኞቹ ካሉባቸው መሰረታዊ ችግሮች ጋር አያይዘውም ” ዩኒቨርሲቲው በአቅራቢያችን የሚገኝ የምርምር ተቋም እንደመሆኑ እና በከብት እርባታ ላይም ልምድ የካበቱ ባለሞያዎች ያሉት በመሆኑ በተሰማራንበት ስራ ውጤታማ በመሆን ወደ ፊት እንዳንራመድ ማነቆ በሆኑብን የዘመናዊ እርባታ ዕውቀት ማነስ ፣ የመኖ ፣የእርባታ ጊደሮች ፤የመድሀኒትና የህክምና ባባለሞያ እጥረትና ጥራት ላይ ከፍተኛ ችግሮች ያሉብን በመሆኑ ዩኒቨርሲቲው ሊያግዘን ይገባል” ሲሉ ጥያቄያቸውን አቅረበዋል፡፡

በመድረኩ የተነሱ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግም የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ም/ት ፕ/ት የሆኑት ፕሮፌሰር ከበደ ወ/ጻዲቅ ዩኒቨርሲቲው አቅሙ በፈቀደ መጠን የወተት ከብት አርቢዎቹ ያሉባቸውን ችግሮች ለመቅረፍ እንዲችሉ ከጎናቸው ቆሞ እንደሚሰራ ገልጸው በተለይም ከእንስሳት ጤና አጠባበቅና ከግንዛቤ እጥረት ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮችን ለመቅረፍ ለነሱም ሆነ በየአካባቢያቸው ላሉ የእስሳት ጤና ባለሞያዎች የአቅም ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት እንደሚሰራ እና በቅርቡም ዩኒቨርሲቲው እያደራጀ ያለው ዘመናዊ የእንስሳት ህክምና ላብራቶሪ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በአካባቢው የሚታየውን የእንስሳት ጤና ችግር ለመቅረፍ ተጨማሪ አቅም እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም ሰልጣኞች ያነሷቸው ከዩኒቨርሲቲው ጋር የተያያዙም ሆኑ ከዩኒቨርሲቲው አቅም በላይ የሆኑ እና የዘርፉ ባለድርሻ አካላት በጋራ ሆነው ሊፈቷቸው የሚገቡ ጥያቄዎችን በተሸለ አቅምና አካሄድ ለመፍታት እንዲቻል በተናጥል ከሚደረጉ ጥረቶች ይልቅ ተደራጅቶ መንቀሳቀስ ችግሮቹን ለመፍታትም ሆነ በዘርፉ ላይ ተወዳዳሪና ብቁ ሆኖ ለመገኘት መደራጀት ተገቢና ከፍተኛ አስተዋጾ ያለው በመሆኑ እራሳቸውን በመዳራጀት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ፕሮፌሰር ከበደ አመልክተዋል፡፡
የስልጠናው ተሳታፊዎችም በርግጥም ተደራጅቶ መስራት አማራጭ የሌለው እንደሆነና ዩኒቨርሲቲው በመደራጀቱ ሂደት ውስጥ ከጎናቸው ሆኖ የሚያግዛቸው ከሆነ እነሱ ተደራጅቶ ለመስራት ፍቃደኛ እንደሆኑ በመግለጻቸው ከስልጣኞችና ከዩኒቨርሲቲው ባለሞያዎች የተውጣጣ አስር አባላትን ያቀፈ አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ የማደራጀት ሂደቱን እንዲያመቻችና ቀጣይ መድረኮችን እንዲዘጋጅ ሀላፊት ተሰጥቶታል፡፡

በመጨረሻም ዩኒቨርሲቲው የወተት ከብት አርቢዎቹን ለማገዝ ከሚሰጠው የስልጠናና የእንስሳት ጤና ህክምና አገልግሎት በተጨማሪ አርቢዎቹ ያሉበትን ተጨባጭ ሁኔታ ቀጣይነት ባለው መልኩ መከታተልና ሞያዊ ድጋፍ መስጠት እንዳለበት በመታመኑ ይህንን ተግባር ሊያካሂድ የሚችል ከኒቨርሲቲው ሀላፊዎች እና ባለሞያዎች የተውጣጣ አንድ የክተትልና ድጋፍ ኮሚቴ በማቋቋም የምክክር መድረኩ ተጠናቋል፡፡