ሐረር ነሐሴ 21/2006 (የኢትዮጵያ ዜና አገልሎት)

የሐረማያ ዩኒቨርስቲ በመጪው የትምህርት ዘመን ከ4 ሺህ 500 በላይ  አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን እንደሚጀምር ገለጸ፡፡

የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ ዛሬ እንደገለጹት በትምህርት ዘመኑ ከነባሮቹ በተጨማሪ የሚቀበሏቸው አዲስ ተማሪዎች በዋናው ግቢ እንዲሁም ሐረርና ጭሮ ከተሞች በሚገኙ ካምፓሶች ነው።

ተማሪዎቹን ተቀብሎ ለማስተናገድ የሚያስፈልጉ መገልገያዎች እያዘጋጁ መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

በተለይ በዋናው ግቢና በሁለቱ ካምፓሶች በመካሄድ ላይ ያሉት የተማሪዎች መማሪያና የመኝታ ክፍሎች በአዲሱ አመት ግንባታቸው ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እንደሚበቁ አስረድተዋል፡፡

እንዲሁም ተማሪዎቹ ወደ ዩኒቨርሲቲው በሚመጡበት ወቅት ችግር እንዳይገጥማቸው የተለያዩ የመስተንግዶ ኮሚቴዎች ተቋቁመው ዝግጅት እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

የሚቀበላቸው አዲስ ተማሪዎች ቁጥር ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር 30 በመቶ ብልጫ እንደሚኖራቸውም  ዶክተር ግርማ ተናግረዋል፡፡

ከዚህም ሌላ መምህራን የማስተማር ክህሎታቸውን እንዲያጎለብቱና የዩኒቨርስቲው ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራ እንዲጠናከር  ለመምህራንና ለአስተዳደር ሰራተኞች የአቅም ግንባታ  ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ገልጸዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በመደበኛ፣በተከታታይ፣በርቀትና በክረምት መርሃ ግብር በቅድመና ድህረ ምረቃ ፕሮግራም ከ34 ሺህ በላይ ነባር ተማሪዎች ያሉት ሲሆን ከእነዚህም 25 ነጥብ 5 በመቶው ሴቶች መሆናቸውን አመልክተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ59 ዓመታት የመማር ማስተማር ስራው 61 ሺህ 757 ተማሪዎችን በተለያዩ የትምህርት መስክ ከዲፕሎማ እስከ ዶክትሬት ድግሪ አሰልጥኖ ማስመረቁን ከዩኒቨርስቲው የተገኘ መረጃን በመጥቀስ የኢትዮጵያ ዜና አገልሎት ዘግቧል፡፡