በተቋሙ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደትን ለማጠናከር የበኩላቸውን እንደሚወጡ አዳዲስ ተማሪዎቹ ተናግረዋል።

ዩኒቨርሲቲው ለ2011 የትምህርት ዘመን የተመደቡ 4ሺ 622 አዳዲስ ተማሪዎችን መቀበል ጀምሯል።

በዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ፣ በነባር ተማሪዎችና በአካባቢው ነዋሪዎች ለተማሪዎቹ ደማቅ አቀባበል እየተደረገላቸው ይገኛል።

ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከመድረሴ በፊት ስሰማ የነበረው ትክክል ያልሆነ እና የታዛበ ነበር ያለው ከደቡብ ክልል ሆሳዕና የመጣው ተማሪ አዱኛ አስፋው የተደረገልን አቀባበል አስደሳች ነው ብሏል።

የመጣሁት ለትምህርት እንደመሆኑ መጠን ዓላማዬን ለማሳካት ተዘጋጅቻለው ሲል ከሰላማዊ መማር ማስተማር ጋር በተያያዘ አስተያየቱን ሰጥቷል።

ከጋምቤላ ክልል የመጣችው ተማሪ ኢክራም መሀመድ በበኩሏ በተቋሙ ማህበረሰብና በአካባቢው ነዋሪ የተደረገልን አቀባበል ከጠበኩት በላይ ሆኖ አግኝቼዋለሁና ቤተሰቦቼ ሃሳብ አይግባችሁ በማለት መልዕክቷን አስተላልፋለች።
ዘንድሮም በዚህ ዓይነት መልኩ ፍጹም ሰላማዊ ሆኖ ትምህርታችንን እንደምናጠናቅቅ እርግጠኛ ነኝ ስትል ተናግራለች።

ተማሪዎች ከአገሪቱ ከተለያዩ አካባቢዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የተለያየ አስተሳሰብ፣ ቋንቋና ሐይማኖት ይዘው ነው የሚመጡት ይህንን በመቻቻል፣ በመከባበርና በመደጋገፍ የመጡበትን ዓላማ ማሳካት ይገባል ያለው ከአርሲ የመጣው ተማሪ ወንደሰን ተስፋዬ ነው።

ከዳውሮ ዞን የመጣው ተማሪ አላዛር ገዝሙ “በአቀባበሉ ደስተኛ መሆኑን ተናግሮ ዓላማዬም መማርና መማር ብቻ ነው፣ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሰራን ለማሳካት የበኩሌን እወጣለው” ሲል ገልጿል።

በአቀባበሉ ስነ ስርዓት ላይ የተገኙተ የአካባቢው ነዋሪ ወይዘሮ አለምጸሀይ ከድር እንደገለጹት አዳዲስ ተማሪዎችን ከነባር ተማሪዎች ከአካባቢው ወጣቶች ጋር በመሆን እየተቀበልን እንገኛለን፤ ይህም ሰላም ፍቅር እና አንድ መሆናችንን ያሳያል ወላጅም ምንም ዓይነት ሃሳብ ሊገባው አይገባም ብለዋል።

የዩኒቨርሲቲው ተወካይ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ ቀደም ሲል ከአካባቢው ማህበረሰብ ፣ ከመምህራን ከአስተዳደር ሰራተኞች ጋር የትምህርት ዘመኑ የተሳካና ሰላማዊ እንዲሆን ውይይት ተደርጎ ከስምምነት ተደርሷል፤
በመማር ማስተማርና በአገልግሎት አሰጣጥ ለግጭት መንስዔ ሊሆኑ የሚችሉ ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ እየተሰራም ይገኛል።

በዚህም መሰረት ዛሬ አዳዲስ ተማሪዎችን ከተቋሙ 20 ኪሎ ሜትር ድረስ ሁሉንም ማህበረሰብን እና ትራንስፖርት በማሰማራት አቀባበል እየተደረገ ይገኛል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘንድሮው የትምህርት ዘመን አዳዲስ ተማሪዎችን ጨምሮ ከ27ሺ በላይ ተማሪዎችን በመደበኛ ፣ በርቀት፣በተከታታይና በክረምት መርሃ ግብር ትምህርት ይሰጣል።