የሆስፒታሉ ተገልጋዮች በበኩላቸው የመድሃኒት አቅርቦትና የጤና ባለሞያ እጥረት ተገልጋዩን ለተጨማሪ ወጪ እየዳረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሆስፒታሉ በሚሰጠው የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ዙሪያ የሆስፒታሉ የስራ ኃላፊዎች ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት አካሂደዋል። በከተማው በሚገኘው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ መሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው የውይይት መድረክ ዩኒቨርሲቲው ሆስፒታሉን ከተረከበ ከሐምሌ 2002 ዓም ጀምሮ ለህዝቡ እየሰጠ የሚገኘውን የጤና አገልግሎት ስራን የኮሌጁ የጤና ሳይንስና የአስተዳደር ልማት ዳይሬክተር አቶ አብዱልባሲጥ ሙሳ ለተሳታፊው በጽሁፍ አቅርበዋል።በተለይ ባለፉት ዓመታት በህብረተሰቡ የሚነሱ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ጨምሮ የንጽህናና ፍሳሽ አወጋገድ፣የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትና የጤና በላሞያ የስነ ምግባር ችግሮች በሆስፒታሉ የስራ አመራር ቦርድና በስራ ኃላፊዎቹ በኩል ችግሩን የመፍታት ስራ ተከናውኗል። ለህሙማኑም ዘመናዊ የጤና አገልግሎትና የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር ህክምና ለመስጠት በሆስፒታሉ ውስጥ ከአንድ ቢሊየን ብር በሚበልጥ ወጪ በመገንባት ላይ የሚገኘው የሪፈራልና የመማርያ ህንጻ ግንባታ ከ90 ከመቶ በላይ መድረሱንና በዚህ ዓመት የመሳሪያ ተከላ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት እንደሚጀምር ተናግረዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል በከተማው የአሚር ኑር ቀበሌ ነዋሪ አቶ አህመድ ዩስፍ በሆስፒታሉ የእናቶችና ህጻናት የጤና አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻል ቢታይም በንጽህና አጠባበቅና በህሙማን እንክብካቤ ስራ ላይ አሁንም ችግሩ አልተቀረፈም።የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትና የጥርስ ሐኪም በሆስፒታሉ አለመኖር ከፍተኛ ወጪ በማውጣት በግል ሆስፒታል ውስጥ አገልግሎቱን እያገኙ እንደሚገኙና ችግሩ እንዲቀረፍላቸው ጠይቀዋል።የቀበሌ 15 ነዋሪ የሆኑት አቶ ዘነበ ወልደጊዮርጊስ በሆስፒታሉ አካል ጉዳተኞችና የአዕምሮ ህሙማን የተለየ የህክምና መስጪያ ስፍራ ባለመኖሩ ህሙማኑ ከመደበኛ ታካሚዎች ጋር ህክምና እንዲያገኙ እየተደረገ በመሆኑ ለህሙማኑም ሆነ ለአስታማሚው ችግር እየፈጠረ ይገኛል።የምሽት የህክምና አገልግሎት የሚሰጠው በመደበኛ የህክምና ባለሞያ ሳይሆን ልምድ በሌላቸው በዩኒቨርሲቲው የጤና ተማሪዎች ስለሆነ በሆስፒታሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ጥራት በከፍተኛ ደረጃ እየታየ እንደሚገኝና ይህም ትኩረት ሊሰጥበት እንደሚገባ አመልክተዋል።

የአቦከር ቀበሌ ነዋሪ ወይዘሮ መቅደስ ግርማ በበኩላቸው የሆስፒታሉ ሰራተኞች መደበኛ የስራ ሰዓትን ጠብቀው ያለመግባትና ከገጠር የሚመጡ ህሙማን በእንክብካቤ ያለመስተናገድ ነዋሪው በአቅራቢያው ወደ ሚገኙ የግል የህክምና መስጪያ ቦታ በመሄድ በአነስተኛ ክፍያ የሚያገኙትን አገልግሎት በከፍተኛ ክፍያ እንዲጠቀሙ እየተገደዱ እንደሚገኙ ገልጸዋል። የሆስፒታሉ ዋና ሜድካል ዳይሬክተር ዶክተር ሬድዋን አህመድ ሆስፒታሉ ከሐረሪና ከፊል ኢትዮ ሶማሌ ክልል፣ከምስራቅ ሐረርጌና ከድሬዳዋ አስተዳደር ለሚመጡ 5 ነጥብ 2 ሚሊየን ለሚሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ከፍተኛና መካከለኛ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል።

ለአገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሆስፒታሉ እያስተናገደ የሚገኘው በርካታ ተገልጋይ መሆኑን ጠቁመው ተሳታፊዎቹ ያነሱትንና ሌሎች በሆስፒታሉ የሚታዩትን የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችንና የግብዓት እጥረቶችን በረዥም፣በመካከለኛና በአጭር ጊዜ ለመፍታትና ለመቅረፍ ቦርዱና አመራሩ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል። በተለይ በሆስፒታሉ የማህጸን ጫፍና የጡት ካንሰር የህክምና አገልግሎት የሚሰጠውና ተኝተው ለሚታከሙ 900 አልጋ ያለው የሪፈራልና የመማሪያ ህንጻ ግንባታ ሲጠናቀቅ ችግሮቹን ሙሉ ለሙሉ እንደሚቀርፍ ገልጸዋል።ትምህርታቸውን ያልጨረሱ ተማሪዎች የህክምና አገልግሎት ይሰጣሉ የተባለው ስህተት እንደሆነና ትምህርታቸውን ጨርሰው ፈተናቸውን አልፈው የመመረቂያ ጊዜያቸውን የሚጠባበቁት ዕጩ ተመራቂ ሀኪሞች ብቻ አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚደረግ ዶ/ር ሬድዋን ጠቁመው ይህም በየትኛውም ዓለም የሚደረግ በመሆኑ ኅብረተሰቡ እንዲያውቅላቸው የመድረኩ ተሳታፊዎች የበኩላቸውን አስተዋፅዖ እንድያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ለአንድ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ የሆስፒታሉ የስራ አመራር ቦርድና ኃላፊዎችን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ የገጠርና ከተማ የኅብረተሰብ ተወካይዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረር ከተማ ለሚገኘው የጤናና ህክምና ሳይንስ ተማሪዎች ለጤና ማስተማሪያና የተሻለ የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለመስጠት ሐምሌ 22 ቀን 2002 ከሐረሪ ክልል መረከቡ ይታወሳል።