ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከ16 ዓመት በላይ ዩኒቨርሲቲውን ላገለገሉት ለዶ/ር መንግስቱ ከተማ አረዶ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ፡፡

ዶ/ር መንግስቱ ከተማ አረዶ ጥር 22 ቀን 1966 ዓ.ም. በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በደገም ወረዳ ልዩ ስሙ ዋጂቱ በሚባል ቦታ የተወለዱ ሲሆን ሙሉ የልጅነት ግዜያቸውን ያሳለፉትና የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በባሌ ዞን ነው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በባሌ ዞን በጎባ ከተማ ተከታትለው በ1982 ዓ.ም. ጨረሱ። ዶ/ር መንግስቱ ከተማ የመጀመሪያ ዲግሪ ትምህርታቸውን ለመከታተል መስከረም 1988 ዓ .ም. ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ገብተው ከዚሁ ዩኒቨርሲቲ በ1991 ዓ.ም. በግብርና ኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በማዕረግ ተመረቁ፡፡ በመቀጠል በኦሮሚያ ግብርና ምርምር ኢንስቲቲዩት ተቀጥረው በሲናና ግብርና ምርምር ማዕከል በጀማሪ ተመራማሪነት ተመድበው ለ2 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ባገኙት የሁለተኛ ዲግሪ የትምህርት እድል በጥቅምት 1994 ዓ.ም ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ገቡ፡፡ በሐምሌ 1995 ዓ.ም. በግብርና ኢኮኖሚክስ በማስተርስ ዲግሪ ተመረቁ፡፡ በዚህ ወቅት የሰሩት የመመረቂያ የምርምር ጽሁፍ በ1996 ዓ.ም. ከቤልጂየም አገር የአለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ሽልማትን አስገኝቶላቸዋል፡፡

የሁለተኛ ዲግሪ ምረቃን ተከትሎ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሌክቸረርነት በ1995 ዓ.ም. ተቀጥረው መስራት ጀመሩ፡፡ በሌክቸረርነት ለ3 ዓመት ተኩል ካገለገሉ በኋላ ባገኙት የስኮላርሺፕ እድል የሶስተኛ ዲግሪያቸውን ለመማር ሰኔ 1999 ዓ.ም ወደ ጀርመን ሀገር ሄዱ፡፡ በጀርመን ሀገር በሚገኘው የጊሰን ዩኒቨርሲቲ ለ3 ዓመት ተኩል ከተማሩ በኋላ በ2003 ዓ.ም በፒ. ኤች. ዲ ዲግሪ ተመርቀው ወደ ሀገር ተመለሱ፡፡ ከተመለሱ በኋላ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መጀመሪያ በረዳት ፕሮፌሰርነት ቀጥሎም በተባባሪ ፕሮፌሰርነት እስከ አሁን እያገለገሉ ይገኛሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲውን ባገለገሉባቸው ጊዜያት በርካታ የትምህርት አይነቶችን በግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ስር በሚገኘው በ”Agricultural Economics and Agribusiness” ትምህርት ቤት ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች አስተምረዋል፡፡ በተጨማሪም ወደ60 የሚሆኑ የሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችንና 15 የሶስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን የመመረቂያ የምርምር ስራቸውን እንዲያከናውኑ በማማከር ለምረቃ አብቅተዋል፡፡ በተጨማሪም ለበርካታ መምህራንን ፤ ለድህረ ምረቃ ተማሪዎች ፤ ለአካባቢው ማህበረሰብና ለዩኒቨርሲቲው በርካታ ጥቅሞችን ያስገኙ የውጭ ፕሮጀክቶችን በማስመጣትና በማስተባበር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪም ከ60 በላይ የምርምር ጽሁፎችን በአለም አቀፍ ጆርናሎች አንዲሁም ወደ 20 የሚሆኑ የምርምር ጽሁፎችን በዎርክሾፕ መጣጥፎች ላይ አሳትመዋል፡፡

ካበረከቱት ሙያዊ አገልግሎት በተጨማሪም ዶ/ር መንግስቱ ከተማ የምርምር ስርጸትና ህትመት ዳይሬክተር በመሆን ከ 7ዓመት በላይ አገልግለዋል፡፡ በዳይሬክተርነት እያገለገሉ በነበሩባቸው ዓመታት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን በተለያዩ የምስራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች ለተጠቃሚዎች በማሰራጨት ፤ የተለያዩ የምርምር ጆርናሎች በዩኒቨርሲቲው ውስጥ እንዲጀመሩ በማድረግ ፤ የተለያዩ ሰነዶችንና መመሪያዎችን ለዩኒቨርሲቲው በማዘጋጀት ፤ እንዲሁም በምርምር ህትመቶች ውስጥ በአርታኢነት በማገልገል ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርከተዋል፡፡ በዚህ ረገድ የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳዮች ጽ/ቤት ላለፉት 7 ዓመታት ላስመዘገባቸው ስኬቶችና ውጤቶች የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡ በተጨማሪም የተለያዩ ኮሚቴዎችን በመምራት ከዩኒቨርሲቲው የተቀበሉዋቸውን ኃላፊነቶች ከግቡ አድርሰዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሴኔትና የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ቦርድ ዛሬ ነሀሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ የዩኒቨርሲቲውን የማዕረግ እድገት መመሪያና ስርአትን በመከተል አስፈላጊውን መስፈርቶች አሟልተው ስለተገኙ ለዶ/ር መንግስቱ ከተማ አረዶ በ‘ግብርናና በሪሶርስ ኢኮኖሚክስ’ ዘርፍ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጥቷቸዋል፡፡