በዞኑ በማህበር የተደራጁ አርሶ አደሮች ከዩኒቨርሺቲው ጋር በመሆን ምርጥ ዘር የማባዛት ስራ ላይ ተሰማርተው ውጤታማ እየሆንን እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት ፕሮጀክት ስራ አስኪያጅ አቶ ደንደና ገልሜሳ “ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲና ከአገሪቱ የተለያዩ የምርምር ተቋማት የተገኙ ምርጥ ዘሮችን በማሳ የተግባር ስራ በማከናወን የመምረጥና የማባዛት ስራ ከአርሶ አደሩ ጋር እየተከናወነ ይገኛል”

በምዕራብና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን በስምንት ወረዳ 38 ቀበሌ ገበሬ ማህበር በሚከናወነው ስራ 3ሺ አርሶ አደሮች በማህበር ተደራጅተው በስንዴ ፣ በቆሎ ፣ ማሽላ ፣ ቦሎቄ እና ሌሎች ምርጥ ሰብሎች ላይ የዘር መረጣና ብዜት ስራ ላይ ተሳታፊ መሆናቸውን ተናግረዋል፤ ከነዚህ ውስጥም 1ሺ 200 ሴት አርሶ አደሮች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ሰብሎቹም የዝናብ እጥረትን እና በሽታን ተቋቁመው ምርት የሚሰጡ መሆናቸውን ጠቁመው በአሁኑ ወቅትም አርሶ አደሩ የሚስማማውን የአዝዕርት ዓይነት እየለየ እና ለሌሎች አርሶ አደሮች ዘሩን እያሰራጨ እንደሚገኝ ጠቁመው በዚህም 23 በዘር ብዜት የተሰማሩ የአርሶ አደር ማህበራት ከፍተኛውን ሚና እያበረከቱ እንደሚገኙ ተናግረዋል።

ባለፉት ጊዜያት ምርጥ ዘሩን ያለምንም የሙከራ ስራ ለአርሶ አደሩ ይሰራጭ ነበር ያሉት አቶ ደንደና የአሁን ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩ በማሳው ላይ ሰብሉን አብቅሎ ውጤቱን በመመልከት የሚበጀውን ለይቶ እንዲመርጥ እየተደረገ በመሆኑ ቴክኖሎጂው ለየት እንደሚያደርገው አስረድተዋል።

በዚህም በዞኖቹ የሚገኙ የዘር አቅራቢ ዩኒየንና ማህበራት፣ ምርጥ ዘር አቅራቢ ድርጅቶች የግብርና ቢሮዎችና ባለሞያዎች ከዩኒቨርሲቲው ተመራማሪዎችና ከቴክኖሎጂው ልምድ እንዲቀስሙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የኩርፋ ጨሌ ወረዳ የግብርና ባለሞያ የሆኑት አቶ ግዛው ልኬለው እንደሚገልጸው ዩኒቨርሲቲው በወረዳው ህዳሴ ፣ ኪንግ በርድና ኦበራ የተባሉ ሶስት የስንዴ ዝርያዎቸ እንዲሁም ከደቡብ ጬንቻ የመጣውን አፕል ዝርያዎችን ከአርሶ አደሩና ከግብርና ባለሞያ ጋር በተግባር ስራ እየመረጥን እንገኛለን።

ተመራማሪው፣ የግብርና ባለሞያና አርሶ አደሩ በጋራ እየሰራን በሚገኘው ተግባር ተኮር የዘር መረጣ የአካባቢውን የዝናብ እጥረት እጥረትን እና በሽታ ተቋቁሞ ምርት የሚሰጠውን ህዳሴ የተባለውን ዝርያ አርሶ አደሩ መርጧል እኛም እንዳየነው ትክክል ሆኖ አግኝተነዋል።

የአፕል ዝርያም ለ16 አርሶ አደሮች ተሰጥቶ ሙከራ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው እንዲህ ዓይነቱ ተግባር ተኮር ቴክኖሎጂ አርሶ አደሩን እያነሳሳ ስለሚገኝ መበረታታት አለበት ብለዋል።

ዩኒቨርሲቲው በተለይ ከሴት አርሶ አደሮች ጋር በሚሰራው ተግባር ተኮር የዘር መረጣ እኛ ሴቶች ተጠቃሚ ሆነናል፤

በአንድ ዓመትም 25 ኩንታል ምርጥ የስንዴ ዘር በማምረት ለአካባቢው አርሶ አደሮች አንዱን ኩንታል በ4ሺ ብር ሸጠናል ያለችው በሜታ ወረዳ ዱርሲቱ ቢሊሱማ ቀበሌ ገበሬ ማህበር በዘር ብዜት ስራ በማህበር የተደራጀችው ሴት አርሶ አደር ሚስራ አደም ናት።

በቀርሳ ወረዳ ወተር ቀበሌ ገበሬ ማህበር በዘር ብዜት ስራ የተሰማራው ሌላው አርሶ አደር ሸረፍ ኡመሬ ከዩኒቨርሲቲው ጋር በቦሎቄ፣ስንዴ ፣ ድንች እና ሌሎች ምርጥ የሰብል ዝርያዎችን በተግባር የምርምር እያመረቱ እና ለአካባቢው ተስማሚ የሆነውን ዝርያ ለሌሎች እያሰራጨን እንገኛለን።

በዚህም ቀደም ሲል ይጠቀሙት የነበረው የድንችና የስንዴ በክረምት ወቅት ብቻ የሚበቅል እና በሽታን የመቋቋም አቅሙ ደካማ እንደነበር ገልጸው በአሁኑ ወቅት ግን በተግባር የሰሩት ኪንግ በርድ የተባለው የስንዴና ቡቡ የተሰኘው የድንች ዝርያ በሽታን ተቋቁሞ የተሻለ ምርት የሚሰጥ በመሆኑ መምረጣቸውን ተናግረዋል፡፡