የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ከሶማሌና ቤኒሻንጉል ክልል ለተፈናቀሉ ወገኖች 192 ኩንታል የምግብ እህል ድጋፍ አደረጉ፡፡

 

የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ከወር ደሞዛቸው ላይ 530,767 ብር በማዋጣት በምዕራብና ምስራቅ ወለጋ እንዲሁም ቦረና ለተጠለሉ ዜጎች ድጋፍ አድርገዋል ፡፡

የዩኒቨርሲቲው መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ያደረጉትንም ድጋፍ ለኦሮሚያ ክልል አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን አስረክበዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲን ወክለው የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴው ሰብሳቢ የሆኑት ዶክተር ኃይለማርያም ከፍያለው እንደተናገሩት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከዋናው የመማር ማስተማር ተልዕኮ በተጨማሪ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ በሆነ አደጋዎች የሚፈጠሩ ችግሮችን ለመቀነስ እንደ ተቋም የሚችለውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል፡፡ የተደረገው ድጋፍም በተለይ በቦረና ፣ ሞያሌ እንዲሁም በምስራቅና ምዕራብ ወለጋ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ችግር ላይ ለወደቁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን ለመርዳት ከመምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች ከደሞዛቸው 530,767 ብር በማዋጣት 60 ኩንታል ፉርኖ ዱቄት ፡ 65 ኩንታል ጨው ፡ 15 ኩንታል በርበሬ ፡ 25 ኩንታል ሽሮ ፡ 27 ኩንታል አተር ክክ በአጠቃላይ 192 ኩንታል እህል በመግዛት እርዳታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

ዶክተር ኃይለማርያም እንደገለፁት የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች በቀጣይነት መንግስትና ህዝብ የጀመሩትን የዜጎችን መብት የማስከበር ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል  ድጋፋቸው የማይለይ መሆኑን ገልጸዋል ፡፡

የተደረገውን ድጋፍ አስመልክቶ የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን የቅድመ ማስጠንቀቂያና የአደጋ ስጋት ቅነሳ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር  አቶ ቤኛ ዱሬሳ በበኩላቸው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ዜጎች ከተፈናቀሉበት የመጀመሪያ ጊዜ አንስቶ መንግስትን በማገዝ የላቀ አስተፅዖ እያበረከተ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በተለይም ከሁለት ዓመት በፊት ዜጎች ከሶማሌ ክልል ሲፈናቀሉ ቀድሞ የደረሰው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ነው ያሉት አቶ ቤኛ እስካሁንም ድጋፋችሁ ሳይለየን ለሶስተኛ ጊዜ ለሌሎች ዓርአያ በሆነ መልኩ ከጎናችን በመሆናችሁ ልባዊ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል፡፡

የኦሮሚያ ክልል የአደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን በአሁኑ ወቅት ከመኖሪያ ቀያቸው ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረግ ፡ ሰላም በአካባቢው የመፍጠርና እንዲሁም መልሶ የማቋቋም ስራን ከሌሎች አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየሰራ ይገኛል ያሉት ዳይሬክተሩ ሁሉም ዜጋ ከግጭት ወጥቶ በሰላምና ልማት ላይ ማተኮር ይጠበቅበታል ብለዋል ፡፡

የኦሮሚያ አደጋ ስራ አመራር ኮሚሽን ከአደጋ ጋር ተያይዞ በሚያደርገው የጥናት ስራ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ለመስራት ፍላጎት ያላቸው መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.