ዜና እረፍት

 

ፕሮፌሰር ተማም ሁሴን አባጨብሳ ከአባታቸው ከአቶ ሁሴን አባጨብሳ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ በድሪያ አባጨብሳ ነሐሴ 12 ቀን 1947 ዓ.ም ጅማ ከተማ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት እንደደረሰ በአካባቢው ባሉ ትምህርት ቤቶች የ1ኛ እና የ2ኛ ደረጃ ትምህርታቸውን አጠናቀው የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በስነ ህይወት ከተመረቁ በኋላ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ሰኔ 30 ቀን 1978 ዓ.ም በመምህርነት ተቀጥረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ተማም ሁሴን

  • የሁለተኛ ዲግሪያቸውን በ(Crop Protection) በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በግብርና ኮሌጅ በ1976 ዓ.ም አጠናቀዋል፤
  • የዶክትሬት ዲግሪያቸውን በአሜሪካ በ Kansas State ዩኒቨርሲቲ በPlant Pathology በ1990 ዓ.ም አጠናቀው ወደ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ተመልሰዋል፡፡

ፕሮፌሰር ተማም ሁሴን

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከተቀጠሩበት  ሰኔ 30 ቀን 1978 ዓ.ም ጀምሮ  እስከ ጥር 1 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ በሌክቸረርነት፣  በረዳት ፕሮፌሰርነት፣ በተባባሪ ፕሮፌሰር እና ፕሮፌሰር ደረጃ  አገልግለዋል ፡፡

በተጨማሪም  ከጥቅምት 22 ቀን 1990 ዓ.ም እስከ ሐምሌ 20 ቀን 1990 ዓ.ም በድህረ ምረቃ ት/ቤት ዲን ሆነው እንዲሁም ከሚያዝያ 17 ቀን 1992 ዓ.ም  እስከ ሰኔ 27 ቀን 1994 ዓ.ም የእፅዋት ሳይንስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡ በእነዚህ ጊዜያትም ኃላፊነታቸውን በብቃትና በታማኝነት  ሲወጡ ቆይተዋል፡፡

በአገር አቀፍና በዓለም ዓቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ የተለያዩ የምርምር ስራዎችን ያሳተሙ ሲሆን የሰብል በሽታዎች ቁጥጥርና መከላከል ላይ ያተኮሩ የስልጠና ፅሁፎችን በማዘጋጀት ለአርሶ አደሮች እና ለግብርና ባለሙያዎች ስልጠና በመስጠት በሙያቸው አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የማስተርስና የፒኤችዲ ተማሪዎችን በማስተማርና በማማከር በአገራችን የተማረ የሰው ሀይል ለማፍራት የሚደረገውን ጥረት የበኩላቸውን አስተዋጽኦ አበርክተዋል፡፡

ፕሮፌሰር ተማም ሁሴን የሁለት ሴቶች እና የአንድ ወንድ ልጅ አባት  የነበሩ ሲሆን በአደረባቸው ህመም ምክንያት በህክምና ሲረዱ ቆይተው በተወለዱ በ63 ዓመታቸው ሐምሌ 19 ቀን 2010 ዓ.ም  ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል፡፡

የቀብር ስነ-ስርዓታቸውም በተወለዱበት በጅማ ከተማ ነገ ሐምሌ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የሚፈጸም ይሆናል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.