የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የስትራቴጂካዊ አመራርና የተቋማዊለውጥዳይሬክቶሬት ከድሬደዋ የስራአመራርና የካይዘን ኢንስቲቲዩት ጋር በመተባበር በካይዘንአመራርሥርዓትአደረጃጀትዙሪያ ለ120 የካይዘን ልማት ቡድን መሪዎች ስልጠና ሰጠ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቁልፍ ተግባራት የተሳኩ እንዲሆኑ ከለውጥ መሣሪያዎች አንዱ የሆነውን የካይዘን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ከከፍተኛ አመራር ጀምሮ በተዋረድ ላሉ አካላት ዩኒቨርሲቲው ግንዛቤ የማዳበር ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛል፡፡ የካይዘን አመራር ፍልስፍና ቀጣይነትና ተከታታይነት ያለው የተሻለ ለውጥ በማምጣት ላይ የተመሠረተ ሲሆን ፍልስፍናውም ከሁሉም በላይ የአመለካከት ለውጥ ለማስረፅ የሚያስችል እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዝደንት ፕሮፌሰር ንጉሴ ደቻሳ በስልጠናው መክፈቻ ላይ እንደገለጹት የካይዘን አመራር ሥርዓት ለተሻለ ለውጥ፣ ጥራትና ምርታማነት የሚያነሳሳና ለተቋማዊ ለውጥ ድርሻው የጎላ ስለሆነ አመራሩንና ሠራተኛውን በማሳተፍ ተግባራዊ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የሥልጠናው ዓላማ የካይዘን ባህሪያትን በመረዳት ከፍተኛው አመራር፣ መካከለኛው አመራር እና ፈጻሚው ሠራተኛ በተደራጀና በተቀናጀ መልክ በመንቀሳቀስ በዩኒቨርሲቲው ፈጣንና ቀጣይነት ያለውን ለውጥ ለማረጋገጥ መሆኑን በስትራቴጂካዊ አመራርና ተቋማዊ ለውጥ ዳይሬክቶሬት የተቋማዊ  ለውጥ ቡድን መሪ ወ/ሮ አበበች ደመላሽ ተናግረዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው የካይዘን ፍልስፍናን ለመተግበር ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን የገለፁት ቡደን መሪዋ የካይዘን ዕውቀትና አሰራሮችን በየደረጃው ለማስረፅ የሚያስችሉ ስልጠናዎችን መስጠት ተቀዳሚ ተግባር በመሆኑ በውስጥ ሠራተኞች መሠረታዊ የካይዘን አሠራር  የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት ወደ ትግበራው ተገብቶ ብዙ አበረታች ለውጦችና ውጤቶች መገኘቱን አስረድተዋል፡፡

የለውጥ ሥራዎችን በተደራጀ ሁኔታ ለማስኬድ መሰል የስልጠና ሥርዓት መዘርጋቱ ትልቅ ፋይዳ እንደሚኖረው በመጠቆም የአፈፃፀሙንም ውጤታማነት በተገቢው መንገድ ለመገምገም እንዲቻል በአደረጃጀቱ ላይ ጠንካራ ተግባራት ሊሠሩ እንደሚገባ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡