ሀረር  ህዳር  27/2009 በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀን መከበሩ ተማሪዎችን እርስ በርስ በማስተዋወቅና ትስስራቸውን በማጠናከር ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን የሚያደርግ መሆኑን የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና ተማሪዎች ተናገሩ።

የዩኒቨርሲቲው ምምህራንና ተማሪዎች 11ኛውን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦችን ቀን በዓል በፓናል ውይይትና በሌሎች ዝግጅቶች አክብረዋል።

ከተሳታፊዎቹ መካከል የዩኒቨርሲቲው የትምህርትና ስነ ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ ዲን ዶክተር ዳዊት ነጋሳ ለኢዜአ በሰጠው አስተያየት፣ ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተሰባሰቡ ብሔር ብሔረሰቦች ባህላቸውንና እሴቶቻቸውን በመለዋወጥ አገራቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ ለማድረስ ቃልኪዳናቸውን የሚያድሱበት ዕለት ነው።

በተለይም በዓሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደረጃ መከበሩ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦችን የሚወክሉ ተማሪዎች ባህሎቻቸውንና እሴቶቻቸውን ከማስተዋወቅ ባለፈ አንድነታቸውን እንዲያጠናክሩ ያደርጋል።

ዶክተር ዳዊት እንዳሉት፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትንሿን ኢትዮጵያን የሚወክሉ እንደመሆናቸው በዓሉ ተማሪዎች ለአብሮነት ተምሳሌት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮችን የሚያንጸባርቁበት መድረክ ነው።

በተማሪዎች መካከል የመቻቻል፣ የመከባበርና አብሮ የመኖርን ባህልን በማጠናከር በተቋማቱ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እንዲሰፍን  በማድረግ በኩል ጠቀሜታው የላቀ መሆኑን ጠቅሰዋል ።

የዩኒቨርሲቲው የህግ መምህር ትግሉ መለስ በበኩላቸው “ህዳር 29 ዜጎች በቋንቋቸው የመጠቀም፣ ሃይማኖታቸውን በነጻነት የመግለጽ፣ ተነፍገው የቆዩትን ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተጎናጸፉበት የድል ቀን ነው” ሲሉ ተናግረዋል።

በዓሉ በከፍተኛ ትምህርት ተቋም መከበሩ አንዱ የሌላውን ቋንቋ፣ ባህልና ወግ እንዲያውቅና በተማሪዎች መካከል የተሻለ ግንኙነት በመፍጠር የመማር ማስተማር ሥራው ሰላማዊ አንዲሆን የሚያደርግ መሆኑን ጠቁመዋል።

በዩኒቨርሲቲው የሁለተኛ ዓመት የህግ ተማሪ ደምሴ የሆነው ታደለ በዓሉ የተለያየ ብሔረሰብ ተዋላጆች አንድነታቸውን የሚያሳዩበትና ግንኙነታቸውን ወደ ተሻለ ደረጃ የሚያሳድጉበት መሆኑን ጠቁሟል።

ተማሪዎች ባህላቸውንና ቋንቋቸውን እንዲለዋወጡ እንዲሁም እርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ባህላቸው ዳብሮ ሰላማዊ ግንኙነት እንዲፈጠር የበዓሉ መከበር ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመልክቷል ።

“በዓሉ ተማሪዎች በተቋም ቆይታቸው ተቻችለውና ተፈቃቅረው እንዲኖሩና አንዱ ሌላውን አክብሮ እንዲኖር ጠቀሜታው የጎላ ነው” ያለው ደግሞ በጋዜጠኝነት ትምህረት የሦስተኛ ዓመት ተማሪ ዘመኑ ለማ ነው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊንኒሳ በወቅቱ እንደተናገሩት፣ የበዓሉ መከበር ዋናው መነሻ በብሔሮች፣ በሔረሰቦችና ሕዘቦች መካከል አንድነትንና መከባበርን ለመፍጠር ነው።

“ህገ መንግስቱም የዜጎችን የማንነት፣ የቋንቋ፣ የሃይማኖትና የእኩልነት ጥያቄ ያረጋገጠና በሀገሪቱ የፌዴራላዊ ስርዓት እንዲመሰረት ያስቻለ ነው ” ብለዋል።

በዓሉም የገዳ ስርዓት በተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ሳይንስና ባህል ድርጅት በአለም የማይዳሰስ ቅርስነት በተመዘገበበት ዋዜማ መሆኑ ልዩ እንደሚያደርገው ተናግረዋል።

በበዓሉ ላይ ከሦስት ሺህ በላይ መምህራን፣ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሠራተኞች የተገኙ ሲሆን በዓሉንና የፌደራሊዝም ሥርአት የተመለከቱ የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቀርበው ውይይት ተደርጎባቸዋል ።