ሃረር ሃምሌ 17/2008 (ኢዜአ) የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በውሃ ጠብታ የእርሻ ስራ ማከናወን የሚቻልበትን ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ነው፡፡
ለከርሰ ምድር ውሃ መዳከም ምክንያት የሆኑ ችግሮችን መቅረፍ በሚቻልበት ዙሪያ በዩኒቨርሲቲው የፓናል ውይይት ተካሂዷል።
የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳይዎች ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ በፓናል ውይይቱ ላይ እንደገለፁት በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል የከርሰ ምድር ውሃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ መጥቷል፡፡

የከርሰ ምድር ውሃ ወደታች በመስረጉም በዩኒቨርሲቲው አካባቢ የሚገኙት የሐረማያ፣ አዴሌና ጢኒቄ ሀይቆች መድረቃቸውን ለአብነት አንስተዋል።
ህብረተሰቡ የመሬት ለምነትን የሚያጎለብቱ የተፋሰስ ስራዎችን ቀደም ባሉ ጊዜያት አለማከናወኑና ውሃን በአግባቡ አለመጠቀሙ ለከርሰ ምድር ውሃ መቀነስ መንስኤ መሆናቸውን ገልፀዋል።
የውሃውን መስረግ ለመታደግ ዩኒቨርሲቲው በዋናው ግቢ የምርምርና በተመረጡ የአርሶ አደር ማሳዎች ላይ በውሃ ጠብታ የእርሻ ስራ ማከናወን የሚቻልበትን ቴክኖሎጂ ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ ይገኛል።
ቴክኖሎጂው አርሶ አደሩ ውሃን ከማሳው ውጪ ያለውን መሬት ሳይሸፍን ለሰብሉ ብቻ የሚጠቀምበት በመሆኑ አረምን ተከላክሎና የውሃ ብክነት ሳያስከትል የተሻለ ምርት የሚያገኝበት መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የፓናል ውይይቱ ዓላማም ይህንን ስራ ማጎልበት ነው ብለዋል።
ቴክኖሎጂውን በምስራቁ የአገሪቱ ክፍል በግብርና ስራ ለተሰማሩ ወጣቶችና አርሶአደሮች ስልጠና በመስጠት የማስፋፋት ስራ በቅርቡ እንደሚጀመር ገልጸዋል።
በፓናል ውይይቱ ላይ ጥናታዊ ጽሁፍ ያቀረቡት የዩኒቨርሲቲው የውሃ ምህንድስና መምህርና ተመራማሪ ሀይሌ አረፋይኔ በ1999 ዓ.ም ሶስት ሜትር ላይ ይገኝ የነበረው የአካባቢው የከርሰ ምድር ውሃ በአሁኑ ወቅት በ12 ነጥብ 5 ሜትር ጥልቀት ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
በዘጠኝ ዓመት ውስጥ 9 ነጥብ 5 ሜትር እየሸሸ ለሚገኘው የከርሰ ምድር ውሃ መንስዔ በቴክኖሎጂ ባልታገዘና ውሃን በማከምና በማጣራት መልሶ ያለመጠቀም ችግር መሆኑን ያሳያል፡፡

የከርሰ ምድር ውሃን በዘላቂነት ለመጠቀም የህብረተሰቡንና የአርሶ አደሩን የውሃ አጠቃቀም በቴክኖሎጂና መልሶ በማከም የመጠቀም ልምድን በስልጠናና በተግባር ስራ ማዳበር አስፈላጊ መሆኑን ጠቁመው ዩኒቨርሲቲውም ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የሐረማያ ወረዳ አስተዳዳር ተወካይ አቶ ከበደ አለማየው በከርሰ ምድር ውሃ እጥረት በአካባቢያቸው የሚገኙ ሶስት ሐይቆች ከመድረቃቸው የተነሳ አርሶ አደሩ በመስኖ የሚያገኘው ምርት እየቀነሰ ይገኛል።
ሐይቆቹን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ቦታ ለመመለስ ለተከታታይ ዓመታት የተፋሰስ ልማት ስራ ቢከናወንም የተፈለገው ውጤት አለመገኘቱን ገልፀዋል፡፡
ችግሩን ለማስወገድ ዩኒቨርሲቲው በዘርፉ ላይ የጀመረውን የጥናትና ምርምር ስራ አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
ላለፉት ሁለት ቀናት በተካሄደው የፓናል ውይይት የዩኒቨርሲቲውን መምህራንና ተመራማራዎችን ጨምሮ ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞንና ከሐረሪ ክልል የተውጣጡ አመራሮችና ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።