የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ሀገራችን የተያያዘችውን የፀረ ድህነት ትግል የሚያግዙ ስራዎችን እያከናወነ መሆኑን የህዝብ ተወካዩች ም/ቤት ቋሚ ኮሚቴ አባላት ገለፁ፡፡ከህዝብ ተወካዮች ሞክርቤት አራት ቋሚ ኮሚቴዎች ውስጥ የተወጣጣ የልዑካን ቡድን ሰሞኑን የዩኒቨርሲቲውን አጠቃላይ የስራ እንቅስቃሴ ገምግሟል፡፡ዩኒቨርሲቲው በመማር ማስተማር በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት እያከናወናቸው የሚገኙ የተለያዩ ስራዎችን የልዑካን ቡድን የጎበኙ ሲሆን ከተማሪዎች ከሠራተኞችና ከተጠቃሚዎችም ጋር የተለያዩ ውይይቶችን አካሂደዋል፡፡

በጉብኝቱ ማጠቃለያ ላይ የቋሚ ኮሚዎቹ ተወካዩች ከዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፈዎች ጋር ባደረጉት የማጠቃለያ ውይይት ላይ የልዑካን ቡድኑ መሪ የተከበሩ አቶ ጌታሁን ብርሃኑ እንደገለፁት ዩኒቨርሲቲው ብቃት ያላቸውን ምሁራን ከማፍራት ጎን ለጎን እያካሄዳቸው የሚገኙት የምርምርና የማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎች ዜጎችን ተጠቃሚ እያደረጉ መሆናቸውን አይተናል ብለዋል፡፡የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የተገኙ የሰብልና የእንስሳት ዝርያዎችን ለተጠቃሚዎች በማድረስ በግብርናው ዘርፍ በሀገራችን የተያዘውን ዕቅድ ለማሳካት የሚያግዝ ስራዎችን በተግባር እያከናወነ እንደሚገኝ የልዑካን ቡድኑ ማየቱንም ገልፀዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍም እያከናወናቸው ከሚገኙ ተግባራት መካከል የአካባቢውን ት/ቤቶች በትምህርት ግብአቶች የመደገፍ፤ ሆስፒታሎችን በህክምና መገልገያ ቁሳቁሶች የማሟላትና ነፃ የህግ ድጋፍ በመስጠት የአካባቢውን ማህበረሰቦች ተጠቃሚ ማድረጉ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎችም በአርአያነት ሊወሰድ የሚገባው ተግባር መሆኑን የተከበሩ አቶ ጌታሁን ብርሃኑ ገልፀዋል፡፡የልዑካን ቡድኑ ከተማሪዎች፣ ሰራተኞችና ተጠቃሚዎች ጋር ባደረጉት ዉይይትና የመስክ ጉብኝት ወቅትም ዩኒቨርሲቲው አፋጣኝ ማስተካከያዎችን ለያደርግባቸው የሚገቡ ጉዳዮችን መለየታቸውን የቋሚ ኮሚቴዎቹ አባላት ገልፀዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ያለውን የአይሲቲ ፋሲሊቲ ከተማሪዎች ቁጥር አንፃር ተመጣጣኝ አለመሆኑ፣ የቴክኖሎጂ ትምህርቶች የተግባር መማሪያ ላቦራቶሪዎች በሚገባው አለመሟላታቸው፣ የመማሪያ ክፍሎች ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች ምቹ አለመሆንን የመሳሰሉት ከታዩ ችግሮች ተጠቃሽ መሆናቸውን በመግለጽ የዩኒቨርሲቲው አስተደደር ችግሮቹን ለማስወገድ በቀጠይ ጊዜያት ትኩረት ስጥቶ ሊሰራበት እንደሚገባ የልዑካን ቡድኑ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ጌታሁን ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡

በአጠቃላይ የልዑካን ቡድኑ የጉብኝት ግኝቶች ላይ በተደረገው ስብሰባ ተለይተው የወጡ ችግሮችን ለማስተካከል ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራበት መሆኑን የአካዳሚክ ጉዳዩች ም/ፕሬዝዳንት ፕ/ር ጨመዳ ፊኒንሳ ጠቁመው የቴክኖሎጂ ካምፓስ ወርክ ሾፕንና የአይሲቲ ፋሲሊቲዎችን አቅርቦት በቀጣዩቹ ሩብ ዓመታት ውስጥ በሚፈለጉበት ደረጃ ለማድረስ እየተሠራ በመሆኑ በዚህ የትምህርት ዘመን ውስጥ ዘላቂ መፍትሄ ያገኛሉ ብለዋል፡፡