የደረቀውን የሀረማያ ሀይቅ ወደ ነበረበት ለመመለስ የህግ ማዕቀፍ ሊኖረው እንደሚገባ የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ ገለፁ፡፡

 

በሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ማዕከል በሀይቁ ተፋሰስ ውስጥ ከሚገኙ ነዋሪዎችና የባለድርሻ አካላት ጋር ሀይቁን ለመመለስ እየተደረገ በሚገኘው ጥረት ዙሪያ ውይይት ተደርጓል፡፡
1
በውይይቱ ላይ ፕ/ር ከበደ ወልደፃዲቅ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ባቀረቡት ፅሁፍ ሀይቁን ለመመለስ እንዲቻል በተፋሰሱ ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ሕብረተሰቡን በማስተባበር እየተሰራ እንደሚገኝና ተስፋ ሰጪ ውጤቶችም እየታዩ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ከዚህም ባሻገር የአካባቢ ጥበቃ ስራው የአካባቢውን ነዋሪዎች ተጠቃሚ ለማድረግ የንብ ማነብ ፤ የዶሮ እርባታና ተያያዥ ስራዎችን አብሮ በማሰራት የኅብረተሰቡን ተሳትፎ ለማሳደግ ዩኒቨርሲቲው ጥረት እያደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
2
ሀይቁን ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላያ ባጋጠሙ ችግሮች ዙሪያ በተደረገው ውይይት ሀይቁ በተወሰነ ደረጃ መመለስ ቢጀምርም ውሀውን ለመስኖ አገልግሎት በመጠቀማቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተመልሶ እንዲጠፋ ምክንያት እንደሆነ ፣ የተወሰኑ ሰዎች ደግሞ ቀድሞ የሀይቁ ክፍል የነበረን ቦታ በመውረር ለእርሻ አገልግሎት በማዋላቸው ሀይቁን ዳግም ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ ችግር እየፈጠሩ መሆናቸውን ተወያዮቹ ተናግረዋል፡፡ ለመሬት ወረራውና ሌሎቹም ችግሮች ሳይባባሱ በአፋጣኝ መንግስት መፍትሄ እንዲፈልግላቸው ተወያዮቹ ጠይቀዋል፡፡

በውይይቱ ላይ የተገኙት የኦሮሚያ ክልል የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ስለሺ ጌታሁን ሀይቁን በሳይንሳዊ መንገድ መመለስ እንደሚቻል በመረጋገጡ የሀይቁን ደለል ለመከላከል የተጀመረው የአካባቢ ጥበቃ ስራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የክልሉ መንግስት በቀጣይ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራበት ተናግረዋል፡፡
3
ውይይቱን የመሩት የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ የሀረማያ ሀይቅ የሀገሪቱን የስነ-ምህዳር ሚዛን ከማስጠበቅ አንፃር ከፍተኛ አስተዋፅዖ ያለው በመሆኑ ተወያዮቹ ያነሷቸውን ችግሮች ቶሎ መፍታት እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡ ችግሮቹን በዘላቂነት ለማስወገድ የሀይቁን ወሰን የማካለልና የማስጠበቅ እንዲሁም የውሀውን አጠቃቀም የሚመራበት የህግ ማዕቀፍ መዘጋጀት እንዳለበት በመጠቆም ወረዳው ጥያቄ አቅርቦ በክልሉ ማፀደቅ ይገባዋል ብለዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.