የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የህሙማን ሪፈራል አላላክና የደም ልገሳ አሰጣጥን ለማሻሻል ከጤና ተቋማት ጋር እየሰራ መሆኑን ገለጸ።

 

የሆስፒታል ጤና ተቋማት ትስስር ላይ ያተኮረ ውይይት በዩኒቨርሲቲው የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ተካሂዷል።

የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የክሊኒካል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሬድዋን ኢብራሂም በዕለቱ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምስራቁ አገሪቱ ክፍል የሚገኙ የጤና ተቋማት የሚከናወነውን የሪፈራል ሲስተምና የደም ልገሳ አሰራርን ለማጎልበት እየሰራ ነው።

ቢሆንም ጤና ተቋማት ቀላል ህክምናዎችንና በተቋሙ መስጠት ሲገባቸው ወደ ሆስፒታል የመላክ እንዲሁም በመጀመርያ ህክምና መደረግ የሚገቡ ህክምናዎችን ሳያካሂዱ  በሪፈራል  መልክ ወደ ሆስፒታል የመላክ ሁኔታ አሁንም እየተስተዋለ ይገኛል።

በደም ልገሳም በኩል እየተከናወነ የሚገኘው ስራ አነስተኛ በመሆኑ በደም እጦት የሚሞቱ የእናቶች ቁጥር አሁንም አለመቀነሱን ገልጸው በቀጣይ በትኩረት ሊሰራባቸው እንደሚገባ ተናግረዋል።

የኮሌጁ የአስተዳደርና ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ቢፍቱ ገዳ በበኩላቸው የሆስፒታል ጤና ተቋማት ትስስር መኖር በጤና ተቋማት የሚታየውን የእውቀት የክህሎትና የሰው ሃይል እጥረቶች እንዲፈቱ ያደርጋል።

እንዲሁም ህመምተኛው ከጤና ተቋም ወደ ሆስፒታሉ በሚላኩበት ወቅት የመጀመርያ ህክምናን ጨምሮ ሌሎችመከናወን የሚገባቸውን ነገሮች ተሟልቶ እንዲላኩ መንገድ ይከፍታል ብለዋል።

በተጨማሪም የግል ሆስፒታል ለህሙማን እየሰጡ የሚገኘው የህክምና አገልግሎት አሰጣጥ ከመንግስት የህክምና ተቋማት ጋር ወጥ የሆነ ስራ እንዲያከናውኑ እገዛ ይፈጥራል ብለዋል።

ተሳታፊዎቹም በጤና ተቋማት የሚሰጡ አገልግሎቶች አሁንም ክፍተት እንደሚታይባቸውና መስተካከል እንደሚገባ አስምረውበታል።

በተለይ የግል ሆስፒታል ላይ የሚታዩ የአሰራር ክፍተቶች አሁንም መፈተሽ እንደሚገባ አምልክተዋል፤ በደም ልገሳ አሰጣጥ ላይ ህብረተሰቡን ያማከለ ስራ ክፍተት መኖሩንና በቀጣይ መሻሻል እንደሚገባው ከስምምነት ላይ ደርሰዋል።

የህይወት ፋና ሆስፒታል የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ነቢል መሀዲ በበኩላቸው በተለይ የሪፈራል አላላክና የደም ልገሳ ስራዎች አሁንም ትኩረት የሚሹ ጉዳይዎች መሆናቸውን አስገንዝበዋል። በግል ሆስፒታል ላይ የሚታዩ ጥቅምን ያማከለ ስራ መቀረፍ እንደሚገባው አስምረውበታል።

ለግማሽ ቀን በተካሄደው የውይይት መድረክ ከምስራቅ ሐረርጌ፣ከድሬዳዋ አስተዳደርና ከሐረሪ ክልል የተውጣጡ የጤና ተቋማት ሃላፊዎችና ባለሞያዎች ተሳትፈዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.