የልማትና የህዳሴው ጉዞን ለማሳካት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ ሰራተኞች ገለጹ

 

ሀረር /ኢዜአ/የካቲት 15/2007

ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን በማጎልበት የሀገሪቱን  የልማትና የህዳሴ ጉዞ  ለማሳካት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የሐረር ጤና ሳይንስ ኮሌጅና የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአስተዳደር ሰራተኞች ገለጹ።

1

ለሰራተኞቹ በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ላይ ለአምስት ቀናት ሲሰጣቸው የቆየው ሰልጠና ትናንት ተጠናቋል፡፡

በውይይቱ ወቅት ከሠራተኞቹ ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች ከሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቲው የስራ ኃላፊዎችና ሌሎች የመንግስት አካላት መልስና ማብራሪያዎች ተሰጥተዋል፡፡

በሰልጠናው ቆይታቸው የሀገሪቱን ቀደምት ታሪክ አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማነጻጸር ልዩነቱንና ለውጡን በሚገባ መገንዘባቸውን ሰራተኞቹ መጨረሻ ላይ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ ላይ አመልክተዋል፡፡

በተለይ አሁን በሀገሪቱ ያለውን ፈጣን የልማት ጉዞ በጠባብና ትምክህተኛ ሃይሎች እንዳይደናቀፍ በመታገል የተጀመረው እድገት ቀጥሎ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት የድርሻቸውን እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

ህገ መንግስቱን በሃይል ለመጣስ የሚሞክሩና ተማሪዎችን የጸብ መነሻ በማድረግ ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማራመድ የሚሞክሩ  የጸረሰላምና ጸረልማት ሃይሎችን ተግባር ነቅተው በመጠበቅ አጋልጠው ለህግ ለማቅረብ ሰራተኞቹ በአቋም መግለጫቸው ላይ ቃል ገብተዋል፡፡

በየመስሪያ ቤታቸው  ኪራይ ሰብሳቢነትና ሌሎችንም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ተቀናጅተው ለማስወገድ የሚያስችላቸውን የአፈጻጸም ሰልትና ግንዛቤ ከስልጠናው ማግኘታቸውና ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ቁርጠኛ መሆናቸውን ጠቁመዋል፡፡

3

ሰራተኞቹ በአቋም መግለጫቸው ላይ እንዳሉት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራን በማጎልበት የሀገሪቱን የልማትና የህዳሴ ጉዞ ለማሳካት ድጋፋቸውን እንደሚያጠናክሩ አረጋግጠዋል፡፡

በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ፍትሃዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውንም አመልክተዋል፡፡

የሐረሪ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ረጋሳ ከፋለ በበኩላቸው ስልጠናው ተማሪዎች የመቻቻልና የመከባበር ባህልን አዳብረው በሀገሪቱ ልማት ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ ሰራተኞቹ ድጋፍ እንዲያደርጉና እንዲያግዙ ትልቅ አቅም እንደሚሆናቸው ገልጸዋል፡፡

በመማር ማስተማሩ ስራ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን ሰራተኛው በዴሞክራሲያዊ አግባብ በመፍታት ረገድ ከስልጠናው ያገኙትን ግንዛቤ ወደ ተግባር በማሸጋገር ለውጤታማነቱ በቅንጅት መንቀሳቀስ እንዳለባቸው አመልክተዋል፡፡

የስልጠናው አስተባባሪ አቶ ሰመረ ተስፋዬ በመንግስት ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ዙሪያ በተሰጠው ስልጠና ከ550 በላይ የሐረር ጤና ሳይንስና ህክምና ኮሌጅ እንዲሁም የህይወት ፋና ሆስፒታል ሰራተኞች መሳተፋቸውን ገልጸዋል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.