ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የተገኘው ቀቀባ የተሰኘው የስንዴ ዝርያ የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ በአጭር ጌዜ ምርት እያስገኘ ነው

 

ሐረር ኢዜአ ጥቅምት 28 ቀን 2009 ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምርምር የተገኘው ቀቀባ የተሰኘው የስንዴ ዝርያ የዝናብ እጥረትን ተቋቁሞ በአጭር ጌዜ  ምርት እያስገኘ ነው ሲሉ በዝናብ እጥረት አካባቢ የሚኖሩ ከፊል አርሶ አደሮችና የልማት ሰራተኞች ተናገሩ።

ዩኒቨርሲቲው በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ዝናብ አጠር በሆኑ ወረዳዎች  ውስጥ በሚገኙ የገበሬ ማሰልጠኛ ማዕከላት ላይ ድርቅን ተቋቁመው ምርት በሚሰጡ የሰብል ዝርያዎች ላይ እያካሄደ የሚገኘውን የምርምር ስራ ግምግሟል።

የጭናክሰን ወረዳም በዞኑ ዝናብ አጠር ከሆኑት አምስት ወረደዋች መካከል አንዱ ነው፤ በወረዳው የምርምር ስራው በሚከናወንበት የመረር ቀበሌ ገበሬ ማህበር ከፊል አርሶ አደር ከዲር አህመድ ጅብሪል በሰጡት አስተያየት ዩኒቨርሲቲው ምርምር አካሂዶበት የሰጠን ቀቀባ የተሰኘው የስንዴ ዘር ድርቅን ተቋቁሞ በቶሎ ምርት ይሰጣል፤ የሰብሉ ዘለላም ረጃጅም በመሆኑ ለከብቶች መኖነት እያገለገለን ይገኛል።

6

 

ከሁለት ዓመታት በፊት እንጠቀም የነበረው የአካባቢው የስንዴ ዝርያ ረጅም ጊዜ የሚወስድና የዝናብ እጥረት ሲያጋጥም ሰብሉ ምንም ዓይነት ምርት ሳይሰጥ ደርቆ ለብልሽት ይዳረጋል።

ቀቀባና መልካሳ ሁለት የተባለወ የስንዴና የበቆሎ ዝርያዎች በድርቅ፣ በንፋስና በበሽታ ሳይጠቁ በአግባቡ ምርት እየሰጡን ይገኛሉ

ከፊል አርሶ አደር አደም ሀሰን በበኩሉ ከዚህ ቀደም የምንጠቀመው የስንዴ ዝርያ የዝናብ እጥረትንና የአካባቢውን ከፍተኛ ንፋስ መቋቋም ስለማይችል ምርት አይሰጠነም።

ከሐረማያ ዩኒቨርሲ በምርምር የተገኘው ቀቀባ የተሰኘው የስንዴ ምርጥ ዘር ግን ድርቅ፣በሽታንና ንፋስን ተቋቁሞ ምርት ከመስጠት ባለፈ ከፍተኛ ውሃን ስለሚወስድ ለምግብነትም  ተመራጭ ሆኗል።

እንደ ከፊል አርሶ አደሮቹ ገለጻ ዩኒቨርሲቲው በምርምር ያገኛቸውን ምርጥ የአዝዕርትና የቅባት እህል ዘሮችን በድጋሚ ከለገሰን የጀመርነውን ምርትና ምርታማነት ማሳደግ እንችላለን ብለዋል።

7

የወረዳው አርብቶ አደር ቢሮ የኤክስቴንሽን ቡድን መሪ አቶ በረከት ተስፋዬ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በወረዳው ገበሬዎች ማስልጠኛ ተቋም ውስጥ ድርቅን ተቋቁመው ምርት በሚሰጡ የተለያዩ የሰብል ዝርያዎች ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር እየሰራን እንገኛለን።

በዚህም በወረዳው ቀቀባ የተባው የስንዴ ዝርያ የዝናብ እጥረትን በመቋቋም ምርት በማስገኘቱና ተመራጭ በመሆኑ በከፊል አርሶ አደሩ  ዘንድ ተፈላጊ ሆኗል፤ የወረዳው አርብቶ አደር ቢሮም ዘሩን ለሌሎች እያስፋፋ ይገኛል።

በቀጣይም የአካባቢውን የአየር ጸባይ ተቋቁመው ምርት የሚሰጡና በገበያ ተፈላጊ በሆኑት የአዝዕርትና የቅባት እህሎች ላይ የምርምር ስራ እየተከናወነ የሚገኝው ስራም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

የዩኒቨርሲቲው የምርምር ጉዳይዎች  ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩስፍ  እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማርና ከማህበረሰብ አገልግሎት ስራ ጎን ለጎን የአካባቢውን ማህበረሰብና የአርሶ አደሩን ፍላጎት መሰረት ያደረገ የምርምርና ስርጸት ስራ እያከናወነና የተገኙትንም ዝርያዎች ለተጠቃሚው ያከፋፍላል።

በአርብቶ አደር ወረዳዎች ላይ በተካሄደው የምርምር ስራ ማህበረሰቡ ቶሎ በመድረስ፣ጥሩ ምርት በመስጠትና በምግብነት ከሌላው ይሻላል ያላቸውን ቀቀባንና ኪንግ በርድ የተባሉ የስንዴ ዝርያዎችን መርጧል።

ዩኒቨርሲቲውም ማህበረሰቡ የመረጣቸውነ የስንዴ ዝርያዎችን የእውቀት ማዕከል በሆኑት የገበሬዎች ማሰልጠኛ ተቋም ላይ በማስፋፋት  ለሁሉም ከፊል አርብቶ አደር የማዳረስ ስራን አጠናክሮ እየቀጠለ ይገኛል።

ዩኒቨርሲቲው፣የልማት ባለሞያውና ከፊል አርብቶ አደሩ በጋራ በቆላ ጥራጥሬና በቅባት እህሎች ላይ እያከናወነ የሚገኘው የምርምር ስራም ውጤቱ ታይቶ ዘሩን የማሰራጨት ስራ እንደሚከናወን ተናግረዋል።

ለምርምር ስራዎቹም መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ የልማት ድረጅቶች አስፈላጊውን ድጋፍ እያደረጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለሁለት ቀናት በተካሄደው የምርምር ግምገማ የልማት ሰራተኞች ፣አርሶ አደሮች፣ ተመራማሪዎች፣መምህራንና ሌሎች መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ መስሪያ ቤት ተወካይዎች ተሳታፊ ሆነዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.