የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሀረር የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ የማስተማሪያ ሆስፒታሉ ውስጥ ከ1ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያስገነባው የሚገኘው ባለ 920 አልጋ የሆስፒታል ህንፃና ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ የሚገኘው የካንሰር ህክምና መስጫ ማዕከል በኢፌዲሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ተጎብኝቷል፡፡

የሆስፒታሉን የግንባታና ተያያዥ ጉዳዮችን በተመለከተ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጨመዳ ፊኒንሳና የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤግዚኪዩቲፍ ዳይሬክተር ዶ/ር ያደታ ደሴ በጉብኝቱ ላይ ለተሳተፉት እንግዶች ገለጻ አድርገዋል፡፡

ከጉብኝቱ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ በሆስፒታሉ ውስጥ እያካሄዳቸው የሚገኙ ግንባታዎች ተጠናቀው ስራ ሲጀምሩ የምስራቅ ኢትዮጵያን ህዝቦች ተጠቃሚ እንደሚያደርግና የሀረር ከተማንም የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከልም እንድትሆን እንደሚያደርጋትና ይህም ተጨማሪ ጠቀሜታ እንደሚሆን ተናግረዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም መንግስት ለሆስፒታሉ የማስፋፊያ ስራዎች መጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ጠቅሰው ወደፊት ይህ ድጋፍ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡