ክለሳ የተደረገባቸው በሶሳተኛ ዲግሪ የአካቶ ትምህርት፤ በሁለተኛ ዲግሪ በልዩ ፍላጎትና በአካቶ ትምህርት የተዘጋጁ ስርዓተ ትምህርቶች መሆናቸውን ኮሌጁ አስታውቋል፡፡

የኮሌጁ ዲን አቶ ገመቹ አበራ ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ እንደገለጹት ኮሌጁ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ስርዓተ ትምህርት ክለሣ ማድረጉን አስታወሰው የአሁኑ ግምገማ ከሌሎች ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የተደረገ ሲሆን ዓለማውም የተማሪዎቹን የትምህርት ተሳትፎና ተግባራዊ ልምድ በማሳደግና የትምህርት ጥራቱን ለማሻሻል የሚያስችል ማስተካከያ ለማድረግ ነው፡፡

የአሁኑ ስርዓተ ትምህርት ክለሳ የሚያተኩረው በነበሩ ስርዓተ ትምህርቶች ላይ የታዩ ከፍተቶችን ለመሙላትና ለማሻሻል ሲሆን ስርዐተ ትምህርቶቹ ለስምንት ዓመት ሳይሻሻሉ የቆዩ በመሆናቸው በጥናት ላይ ተመርኩዘው ለማሻሻል መሆኑን አቶ ገመቹ ተናግረዋል፡፡

የነበሩ አስር ስርዓተ ትምህርቶችን ከወቅቱ ቴክኖሎጂ ጋር አዋህዶ ጊዜው የሚፈልገውን እውቀት ለማስጨበጥ እንዲችሉ አንድ ዓመት ባልሞላ ጊዜ ጥናቶች ተካሂደው እንዲገመገሙ ማድረጋቸውን ዲኑ ገልፃዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ተወካይ ዶክተር ይልፋሸዋ ስዩም በመከፈቻ ንግግራቸው ኮሌጁ የነባሩን ከሚሰጣቸው ነባር ስርዓተ ትምህርቶች ዘጠና በመቶ የሚሆኑት ላይ ክለሳ ማድረጉንና ሁለት አዳዲስ የድህረ-ምረቃ ትምህርቶችንም ከተቋሙ ተልዕኮና ስትራቴጂክ ዕቅድ ጋር አዛምዶ ተራማጅ የሆነ ትውልድ ለማፍራት የሚያስችል የስርዓተ ትምህርት ዝግጅት ማካሄዱን አስታውቀዋል፡፡

የክለሳ ሠነዶቹ ከፍላጎት ዳሰሳ ጀምሮ በደንብ የተደራጀና ሌሎች ግንኙነት ያላቸው ሰነዶችንም ተካተውበት በሚገባ ተጣጥሞ የተዘጋጁ በመሆኑ ከባህርዳርና ከአዲስ አባባ ዩኒቨርሲቲዎች የዘርፉ ባለሙያዎችን እንዲገመገሙት ተደርጎ ለሀገራዊ ውይይት መቅረቡን ዶክተር ይልፋሸዋ አስታውቀዋል፡፡

ክለሣ የተደረገባቸው በሶሳተኛ ዲግሪ የአካቶ ትምህርት፤ በሁለተኛ ዲግሪ በልዩ ፍላጎትና በአካቶ ትምህርት የተዘጋጁ ስርዓተ ትምህርት ሠነዶች መሆናቸውንና በዘርፉ ምሁራን ግምገማና ውይይት ተደርጎባቸዋል ሲል ሲሳይ ዋቄ ዘግቧል፡፡

ፎቶግራፈር ፡- ፎአድ አህመድ