በማዕከሉ እንቅስቃሴም ዙሪያ ዛሬ ጥር 8/2013 ዓ.ም በሐረር ከተማ ውይይት ተደርጓል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ በምስራቅ ኢትዮጵያ የመጀመሪያውን ሐረር ሚ-ኬር Harar ME-CCARE አምቡላንስ ስምሪት ማዕከል በሐረር ከተማ ከፍቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል። የስምሪት ማዕከሉ መከፈትም የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ዘርፍ ያሉበትን ችግሮች ለማሻሻል ትልቅ አስተዋጽዎ ይኖረዋል ተብሏል።

በአጭር የስልክ ቁጥር 7605 በመጠቀም የድንገተኛ እና የፅኑ ህክምና አገልግሎትና ዘመናዊ ቅድመ ሆስፒታል አገልግሎት ማግኝት እንደሚቻልም በሐረር ሚ-ኬር የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም በተከናወኑ ስራዎች ዙሪያ በተካሄደ ውይይት ላይ ነው የተገለፀው።

በድንገተኛና ፅኑ ህሙማን እንክብካቤ ማሻሻያ ፕሮግራም የተሰሩ ስራዎችን የዩኒቨርሲቲ ሆስፒታሉ ቺፍ የአስተዳደርና ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር ኢብሳ ሙሳ አቅርበው ውይይት ተካሂዷል። የመድረኩ ተሳታፊዎችም የኮሌጁ አመራር ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት በዚህ አጭር ግዜ ውስጥ በርካታ ስራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።

የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤክዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር ያደታ ደሴ እንደገለጹት

እስካሁን ያለው አፈፃፀም መልካም መሆኑን ጠቁመው ፕሮግራሙ ዜጎች ሆስፒታል ደርሰው ተገቢውን ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው እንዳያልፍ የሚያግዝ መሆኑን አስረድተዋል።

ለድንገተኛ አደጋ የሚያገለግል የአንድ ማዕከል አምቡላንስ አገልግሎት በማስጀመር ለሐረር እና አካባቢው ማህበረሰብ አገልግሎት መስጠት መጀመራቸውንም ዶ/ር ያደታ ተናግረዋል።

ሐረር ሚ-ኬር ፕሮግራም የምስራቁን የሐገራችን ክፍል የድንገተኛ እና የፅኑ ህክምና አገልግሎት ስራ አቀናጅቶ ለመስራት እንዲያሥችል በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ አስተባባሪነት የሐረሪ ክልል ጤና ቢሮ ፣ የሐረር ከተማ ማዘጋጃ ቤት እና ምስራቅ ሐረርጌ ዞን መስተዳደርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በጋራ በጥምረት የተጀመረ ፕሮግራም ነው።

የውይይቱ ተሳታፊዎችም ማዕከሉን መጎብኘታቸውን ከጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።