ፕሮግራሙ ሐረርን ጨምሮ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል በተቆራረጠ ሁኔታ የሚከናወኑ የድንገተኛ አደጋና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና አገልግሎት አሰጣጥ ወጥና ተቋማዊ እንዲሆን እንደሚያደርግ ተመልክቷል።

ሐረር ሚ-ኬር (Harar emergency Medical & critical care /HARAR ME-CCARE) ፕሮግራምን ትናንት በይፋ ያስጀመሩት የሐረሪ ክልል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኦርዲን በድሪና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወልዪ ናቸው።

ፕሮግራሙ በሐረሪ ክልል እና በምስራቅ ሐረርጌ ዞን የድንገተኛ እና የፅኑ ህክምና አገልግሎቶችን ለማቀላጠፍ የተቀረጸ መሆኑን በሥነ ሥርዓቱ ላይ ተገልጿል።

የሀረሪ ክልል ፕሬዚዳንት አቶ ኦርዲን በድሪ ፕሮግራሙ መጀመሩን ይፋ ሲያደርጉ ባደረጉት ንግግር የድንገተኛ እና የፅኑ ህክምና አገልግሎቶች ሰው ኃይልና የቴክኖሎጂ ውስንነት ያለበት ዘርፍ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሆኑም ፕሮግራሙን በተቀናጀና በተደራጀ መልኩ በሚፈለገውና በሚጠበቀው ደረጃ ለማሳካት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር በባለቤትነትና በኃላፊነት እንሚሰራ አረጋግጠዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳሉት በሀገር አቀፍ ደረጃ ከተመረጡ አምስት የድንገተኛና ጽኑ ህሙማን እንክብካቤና ማሻሻያ አገልግሎት መስጫ ፕሮግራሞች መካከል የሐረሩ አንዱ ነው።

የድንገተኛና ፅኑ ህሙማን ህክምና አገልግሎት ከዚህ ቀደም ትኩረት ያልተሰጠውና ክፍተት የነበረበት መሆኑን ጠቁመው በአሁኑ ወቅት ግን ለህብረተሰቡ ተደራሽ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን አቶ ኦርዲን ተናግረዋል።

ሆስፒታሎችና ሌሎች ጤና ተቋማት በአገልግሎቱ አሰጣጥ የሚታዩ ክፍተቶችን በቴክኖሎጂ፣ ሰው ኃይል እና ግብአት የማጠናከር ስራ ይከናወናል፤ የክልሉ መንግስትም አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል ብለዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሐረር ህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲቺንግ ሆስፒታል ውስጥ ከ1000 በላይ የህሙማን አልጋ የሚኖረው ዘመናዊ የህክምና ማዕከል ግንባታን እያጠናቀቀ መሆኑ ለምስራቅ ኢትዮዽያ የተሻለ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙ ከማስቻሉ ባሻገር ሐረርን የህክምና ቱሪዝም ማዕከል እንደሚያደርጋት አቶ ኦርዲን ተናግረዋል።

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ ቺፍ ኤግዚኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ያደታ ደሴ በበኩላቸው ድንገተኛ አደጋዎች በተሸከርካሪ ፣ እሳት ፣ ግጭትና በሌሎችም ሰው ሰራሽና ተፈጥሮ ችግሮች የሚከሰቱ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በዚህ ምክንያት ችግሮቹ ሲከሰቱ ፕሮግራሙ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ለሚገኝ ህዝብ በህይወት ፋና ሆስፒታል አገልግሎቱን ለመስጠት ስራውን በይፋ መጀመሩን አስታውቀዋል።

ምስራቅ ሐረርጌ የተሸከርካሪ አደጋ የሚበዛበት ዞን መሆኑን የገለጹት ደግሞ የዞኑ ጤና ጥበቃ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ አብዱረሃማን በበኩላቸው የፕሮግራሙ መጀመር ያለውን ሀብት አሥተባብሮ በመጠቀም በአደጋ ጉዳት የሚደርስባቸውን ሰዎች ለመታደግ ጠቀሜታው የጎላ ይሆናል ብለዋል።

በፕሮግራሙ ማጠቃለያ ላይ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደርና ተማሪዎች ጉዳይ ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጄይላን ወሊዪ ባደረጉት ንግግር ህንፃን ልጅን ማሳደግና ተቋም የመገንባት ሥራ ጥንቃቄንና የብዙ አካላት ርብርብ የሚጠይቅ በመሆኑ በዩኒቨርሲቲያችን የሚቋቋመው የድንገተኛና ፅኑ ህክምና መስጫ ማዕከል ውጤታማ እንዲሆን ዩኒቨርሲቲያችን ከፍተኛ ጥረት የሚያድረግ በመሆኑ ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላትም የበኩላቸውን ኃላፊነት በቁርጠኝነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ ዘርፎች በምሥራቅ ኢትዮጵያ የሚኖሩ ሰዎችን ችግሮች በመፍታት ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ፕሮፌሰር ጄይላን ጠቁመው በጤናው ዘርፍ የተሻለ አገልግሎት ለህዝቡ ለማድረስ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ ከፍተኛ በጀት የጠየቀውን የሆስፒታል ግንባታ እያጠናቀቁ እንደሆነና ትናንት ይፋ የተደረገውም ፕሮግራም በተለያዩ ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ዜጎችን ህይወት ለመታደግ ያሥችላል ማለታቸው የሐ.ዩ. ማህበረሰብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 91.5 ባልደረባ ዘግቧል።