የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ 355 ዕጩ ተመራቂ ተማሪዎች “የማህበረሰባችንን ውለታ ለመመለስ እንሰራለን” በሚል መሪ ቋል የመስክ የቡድን ስልጠና ሊወስዱ ነው።

የቡድን ስልጠናው /Team Training Program TTP / በሐረሪ ክልል በተመረጡ 9 ቦታዎች ላይ ለአምስት ሳምንት የሚቆይ ሲሆን ከዛሬ ጥር 3 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ እንደሚጀመር የኮሌጁ የህብረተሰብ አቀፍ የተግባር ስልጠና አስተባባሪ አቶ ደጉ አባተ ገልጸዋል።

አስተባባሪው ዛሬ በሰጡት መግለጫ የማህበረሰቡን የጤና ችግር በመለየት ለሀገሪቱ የጤና ልማት መርሀ-ግብሮች ተፈጻሚነት የህብረተሰብ አቀፍ የተግባር ስልጠና ትምህርት ወሳኝ መሆኑን ገልጸዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች አገራዊና አካባቢያዊ ይዘት ያላቸው ፍላጎትን መሰረት ያደረጉ ችግር ፈቺ የማህበረሰብ አገልግሎት በተመደብበት ቦታዎች ላይ እንደሚሰጡ ገልጸዋል።

ተመራቂ ተማሪዎች በተግባር ስልጠና ቆይታቸው የአካባቢና ማህበረሰብን የጤናና ተያያዥ ችግሮችን የመለየት ፣ የኮቪድ -19 ቅድመ ጥንቃቄ እንዲሁም የአነስተኛ ፕሮጀክት ጽንሰ ሀሳብ በመቅረጽ መፍትሄ መስጠትን ላይ የሚያተኩር ስልጠና መሆኑን ገልጸዋል።

የኮሌጁ መምህራን ከማስተማር ባለፈ ወደ ጤና ተቋማት ወርደው ስልጠናውን መስጠታቸው በጤና ተቋማት ላይ ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽዖ እንደሚኖረው አብራርተዋል።

በአሁኑ ወቅት የኮቪድ-19 ሥርጭት ቁጥሩ በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ ቢመጣም ኅብረተሰቡ አሁንም የበሽታው የመከላከያ መንገዶች አተገባበር ላይ መዘናጋት እያሳየ እንደሚገኝ ገልጸው የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት ኅብረተሰቡ ከዚህ ቀደም ሲተገብረው የነበረው የመከላከሉን ተግባር በትኩረት ሊፈጽም እንደሚገባ አስታወቀዋል።

የኮሌጃችን ተመራቂ ተማሪዎች ልክ እንደከዚህ ቀደሙ ሁሉ በሰላማዊ መማር ማስተማር ረገድ የሰላም አምባሳደርነታችንን በዘላቂነት ማረጋገጥ ፣ ለህብረተሰቡ ፋይዳ ያላቸዉን ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማካሄድ ለሌሎች ተምሳሌት በመሆን ፣ ተግተው በመማር ፣ በቅርብ ዓመታት ዉስጥ የኮሌጃችንን ራዕይ በማሳካት ለሀገራችን ሁለንተናዊ እድገት ከፍተኛ ሚናችሁን እንድትወጡ ሲሉ አቶ ደጉ ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የመስክ የቡድን ስልጠና Team Training Program /TTP / በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን በመጀመሪያ ዙር የጤና ሳይንስ ተመራቂዎች እንዲሁም በሁለተኛ ዙር ላይ የህክምና ተመራቂ ተማሪዎች እንደሚሰጥ ከኮሌጁ ያገኝነው መረጃ ያመለክታል።