ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያሰራጫቸው ሰባት የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎች በገቢያቸው ላይ ተጨባጭ ለውጥ ማምጣቱን የባቢሌ ወረዳ አርሶ አደሮች አስታወቁ፡፡

ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ወረዳዎች ውስጥ ለስድስት ሺህ አርሶ አደሮች ሶስት ሚሊዮን የስኳር ድንች ችግኝ ማከፋፈሉንና አርሶአደሮቹ ያመረቱትንም ስኳር ድንች መልሶ እየገዛቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡

የዓለም አቀፍ ድንች ማዕከል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር እያሰራጨ ያለው የተሻሻሉ የስኳር ድንች ዝርያዎች በተለያዩ የምግብ ነጥረ ነገሮች የበለጸጉ እንደመሆናቸው ለነፈሰጡሮች ፣ ለጎልማሶችና ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህጻናት እጅጉን ጠቃሚ መሆናቸውን ከማዕከሉ የተገኘው መረጃ ያመላክታል።

በባቢሌ ወረዳ በቢሻን ባቢሌ ገጠር ቀበሌ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 91.5 ካነጋገራቸው አርሶአደሮች መካከል ሼክ መሀመድ ዩሱፍ እንደገለጹት አካባቢው በአቀንጭራ አረም ከሚጠቁት ቦታዎች አንዱ በመሆኑ ቀደም ሲል ከዚህ መሬት ምንም ምርት አግኝተውበት አያውቁም ነበር፡፡

በያዝነው የምርት ዘመን ግን የባለሙያዎች ምክርን በመስማት ዲላ የተባለ የተሻሻለ የስኳር ድንች ዝርያን ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ወስጄ በመተከሌ ከ80 ኩንታል በላይ ምርት አግኝቻለሁ ፤ ዩኒቨርሲቲው ከዚህ ምርት ውስጥ አርባ (40) ኩንታል አንዱን በሁለት ሺህ ብር ሂሳብ መልሶ በመግዛት የገበያ ትስስሩንም አሳምሮልኛል ብለዋል፡፡

በአራት ጥማድ መሬት ላይ ብቻ ካመረትኩት 80 (ሰማኒያ) ኩንታል 160 ሺ (መቶ ስድሳ ሺህ) ብር ገቢ አግኝቻለሁ ፣ ከእኔ ሳይለዩ ሙያዊ ድጋፍ ላደረጉልኝ ፣ ዘሩን ለሰጡኝና የገበያ ትስስሩን ለፈጠረልኝ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ምስጋና አቀርባለሁ ብለዋል ሼክ መሀመድ ዩሱፍ ፡፡

የግብርና ቴክኖሎጂን ተጠቅመው ያገኙትን ምርት

ከባለቤታቸውና ከልጆቻቸው ጋር ሲሰበስቡ የሐ.ዩ. ኤፍ ኤም ዘጋቢ ያናገራቸው ወይዘሮ አሊያ ቃሲም እንደገለጹት ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ያገኘነው አዲሱ ስኳር ድንች በኑሮአችን ተጨባጭ ለውጥ አምጥቷል ፤ አሁን ከእኔ የሚጠበቀው ለቀሩት ወገኖቼ እውቀቱን ማስተላለፍና ማሰተማር ነው ብለዋል፡፡

የግብርና ልማት ሰራተኛው አቶ አቂል አብዱለጢፍ በበኩላቸው አርሶአደሩ ስኳር ድንች የደሃ ምግብ ነው ብለው ስለሚያምኑ በመጀመሪያ የሰራነው በሰው አዕምሮ ለይ ነበር። አስተሳሰቡ ትክክል እንዳልሆነና በንጥረ ነገር የበለጸገ ፣ በአቀንጭራ አረም አለመያዙን ፣ ድርቅን መቋቋም መቻሉን ፣ በአጭር ጊዜ መድረሱንና ከፍተኛ ምርት መስጠቱን ካሳመንን በኋላ ዘሩን ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ አምጥተን ተክለን ምርታማነቱንና አዋጭነቱን ማሳ ላይ ካረጋገጥን በኋላ ለአርሶአደሩ እንዲደርስ አድርገናል ብለዋል።

 

አቶ አቂል አክለውም ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመሆን ከምስራቅና ምዕራብ ሐረርጌ ዞኖችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ምርቱን በተለያዩ መንገዶች መጠቀም እንዲችሉ ልምድ ለመለዋወጥ የአርሶ አደሮች ሰርቶ ማሳያ የመስክ ቀን ተዘጋጅቶ ከሃያ በላይ ከስኳር ድንች የተዘጋጁ የምግብ ዓይነቶች ተዘጋጅተው ለእይታ ቀርቧል ብለዋል፡፡

የቢሻን ባቢሌ ገጠር ቀበሌ ሊቀመንበር አቶ አሊ አሜ ለሐ.ዩ. ኤፍ ኤም እንደተናገሩት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ላለፉት 3 ዓመታት አርሶ አደሮች ደረጃውን የጠበቀ ምርጥ ዘር አምርተው ለገበያ እንዲያቀርቡ ከማድረጉም በተጨማሪ በምግብ ንጥረ ነገር የበለጸገና በገበያ ላይ ተፈላጊ የሆነውን የተሻሻለ የስኳር ድንች ዝርያ ስለሰጠን በባቢሌ አርሶአደሮች ስም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የዓለም ድንች ማዕከል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ክላስተር ኃላፊ ዶክተር ደንዳና ገልሜሳ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በዘጠኝ የምስራቅና የምዕራብ ሐረርጌ ወረዳዎች ውስጥ ለስድስት ሺህ አርሶ አደሮች ሶስት ሚሊዮን የስኳር ድንች ችግኝ ያከፋፈለ መሆኑንና በቀጣይም አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል ሲል ሲሳይ ዋቄ ዘግቧል።