ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከ10 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመቱ የህክምና ቁሳቁሶችና የአንበጣ መከላከያ ድጋፍ አደረገ

ሐረር፣ ጥቅምት 19/2013(ኢዜአ) ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ 10 ሚሊየን ብር ግምት ያላቸው ለህክምና አገልግሎትና የአንበጣ መንጋ ለመከላከልና የሚውሉ ቁሳቁሶችን ለአካባቢው ግብርና ጽህፈት ቤቶችና ሆስፒታሎች ድጋፍ አደረገ።

በድጋፉ አሰጣጡ ስነ ስርዓት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር ጀማል የሱፍ እንደተናገሩት ተቋሙ የአንበጣ መንጋ ከተከሰተ ጀምሮ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በባህላዊና ሳይንሳዊ ዘዴ የመከላከል ስራ ሲያከናወን ቆይቷል።

ባለሙያዎችን በመመደብ በእውቀት የታገዘ የመከላከል ስራ እያከናወነ መሆኑን ጠቁመው፤ በቀጣይም በጥናትና ምርምር የታገዘ ስራ እንደሚያካሄዱ ገልጸዋል።

ከድጋፉ መካከል ለሐረማያና ህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ቲቺንግ ሆስፒታል የሰጡት የህክምና ቁሳቁስ የአሜሪካው ክርስቲያን ሪሊፍ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት የተገኘ መሆኑን ዶክተር ጀማል አስረድተዋል።

ከህክምና ቁሳቁሶቹ ውስጥ የልብ መመርመሪያ ማሽን፣ መካኒካል ቬንትሌተር፣ ኤክስ ሬይ ማሽን ፣ለቀዶ ህክምናና ለኮሮና መከላከያ የሚያገለግሉ መሳሪዎች ይገኙበታል።

በዩኒቨርሲቲው የአንበጣ መከላከል ግብረ ሃይል አባል ዶክተር ደንደና ገልሜሳ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲው የአንበጣ መንጋን ለመከላከል ግብረ ሃይል አቋቁሞ ከምስራቅ እና ምዕራብ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤቶች ጋር እየሰራ ነው ብለዋል።

 

በተጨማሪም ባለሙያዎችን በየወረዳው መድበው መንጋውን ለመከላከል እያገዙ መሆኑን ጠቁመው፤ አሁን ደግሞ በሞተርና በሰው ሀይል የሚሰሩ የአንበጣ መከላከያ ኬሚካል መርጪያ መሳሪያዎችና ለዚህ ተግባር የሚያገለግሉ አልባሳት ለሁለቱ ዞኖች ግብርና ጽህፈት ቤቶች መሰጠቱን ተናግረዋል።

የምስራቅ ሐረርጌ ዞን ግብርና ጽህፈት ቤት ተወካይ አቶ አብዲ ኢብራሂም እንደተናገሩት በዞኑ 17 ወረዳዎች በሚገኙ 290 ቀበሌዎች ውስጥ በተከሰተው የአንበጣ መንጋ 104 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የለማ ሰብል ላይ ጉዳት አድርሷል።

ከአርሶ አደሩና ሌላውም ማህበረሰብ ጋር በመሆን በባህላዊና ኬሚካል ርጭት የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው ፤ በተለይ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ጋርም ስራውን በቅንጅት እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በተደጋጋሚ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ለሆስፒታሉ ያደርግልናል ያሉት ደግሞ የሐረማያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሰለሞን ታምራት ናቸው።

በተለይ አሁን ዩኒቨርሲቲው ያደረገላቸው የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ በሀገር ውስጥ በቀላሉ የማይገኙና ከኮሮና ጋር በተያያዘ ለሚከናወነው የህክምና አገልግሎት ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ተናግረዋል።