ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከአንድ ዓመት በፊት በስራ ላይ እያለ ሁለት እጆቹን በአደጋ ምክንያት ላጣ ሠራተኛው ባለ ሶስት እግር ተሽከርካሪ በእርዳታ ሰጠ፡፡

የዩኒቨርሲቲው ቋሚ ሠራተኛ የሆነው መሐመድ አደም ዑመር መደበኛ ሥራው የከብት መኖ ማዘጋጀት (silage) ሲሆን መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ/ም የመኖ ዝግጅት ሥራውን በማከናወን ላይ ሳለ እየሰራበት የነበረው ማሽን ልብሱን ሲይዝበት ለማስለቀቅ ባለመቻሉ ጎትቶ ሁለቱንም እጁን እንደቆረጠበት የሚናገረው መሐመድ አደጋው በደረሰበት ወቅት ራሱን ስቶ ራሱን ከሁለት ቀን በኋላ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እየተደረገለት እንደነቃ ይናገራል::

በአደጋው ምክንያት እርሱም ሆነ ቤተሰቡ ከፍተኛ ሀዘን እንደደረሰባቸውና ተስፋ መቁረጥ ውስጥ እንደከተታቸው የሚናገረው መሐመድ ዩኒቨርሲቲው አደጋው ከደረሰበት እለት አንስቶ ከህክምና ወጪ ባሻገር ባደረገለት ሁለንተናዊ ድጋፍና እንክብካቤ የደረሰበትን ተጽዕኖ ተቋቁሞ ዛሬ ላይ በመድረሱ ደስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡

በድጋፍ የተሰጠው ተሽከርካሪ ቁልፍ ርክክብ ወቅት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ እንደተናገሩት መላው የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ በደረሰው አደጋ ማዘኑን ተናግረው ምንም እንኳን ከጉዳቱ ጋር የሚመጣጠን ባይሆንም አደጋው ከደረሰበት ዕለት አንስቶ ይህን ሚኒዶር (ፎርስ) ተሽከርካሪን ጨምሮ በተቻለው አቅም ቤተሰቡን ለመርዳት ጥረት መደረጉን ጠቁመው በቀጣይም የሰው ሰራሽ እጅ ገጠማና ሌሎች ድጋፎች እንደሚደረግለት ቃል ገብተዋል፡፡

በድጋፍ የተሰጣቸው ሚኒዶር (ፎርስ) ተሽከርካሪ እርሱንና የቤተሰቡን ኑሮ ለመደገፍ እንደሚረዳቸው የተናገረው አቶ መሐመድ ተስፋዬ በጨለመ ጊዜ ከጎኔ ቆሞ ለደገፈኝና አለሁ ላለኝ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምስጋናዬን አቀርባለሁ ፣ የዩኒቨርሲቲው ሠራተኛም በመሆኔ ከፍተኛ ኩራት ይሰማኛል ብሏል፡፡

አቶ መሐመድ የሁለት ህጻናት ሴት ልጆች አባት ነው፡፡