በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ምርምር ጉዳዮች ምክትል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የዘር ስርጭት ባለሙያ አቶ ተክለማሪያም ቀነኒ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው በምርምር የተገኙ የእንስሳት ፣ የሰብል ፣ የአትክልትና ፍራፍሬ ዝርያዎችን እያሰራጨ ኅብረተሰቡን የቴክኖሎጂ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን ጠቁመው በትናንትናውም እለት በኢፋ ኦሮሚያ ፣ በኩሮና በአሙማ የገጠር ቀበሌዎች ውስጥ ለ75 እማወራ አርሶ አደሮች ዝርያቸው የተሻሻለ አውራ የዶሮዎችን አከፋፍለናል ብለዋል።

በሐረማያ ዩነቨርሲቲ መምህርና የእንስሳት ተመራማሪ የሆኑት አቶ እውነቱ ከበደ በበኩላቸው የኒቨርሲቲው ከዛሬ ሀምሳ ዓመት በፊት ከባህር ማዶ የተሻሻሉ የተለያዩ የዶሮ ዝርያዎችን ወደ ሀገር ማስገባት መጀመሩን ገልጸው የአሁኖቹ ዶሮዎች ቀደም ሲል ከግብጽ ካስመጣናቸው ዶሮዎች ጋር በማዳቀል የተገኙ የስጋ ምርታማነታቸው ከፍተኛ መሆኑን በምርመር አረጋግጠን ለኅብረተሰቡ አከፋፍለናል ብለዋል።

አቶ እውነቱ እንደገለፁት የዶሮቹ አያያዝ ፣ አመጋገብና ጤና አጠባበቅ ለተጠቃሚዎቹ ትምህርት መሰጠቱንና ወንድ ዶሮ የተከፋፈለበት ምክንያት ሴት ዶሮ ጥቅሟ ለግለሰብ ብቻ በመሆኑ ሰፈሩ በሙሉ ተጠቃሚ እንዲሆን በማሰብ ሴት ዶሮዎችን እንዲያጠቃና ዝርያውን እንዲስፋፋ ለማድረግ ነው ብለዋል፡፡

የኢፋ ኦሮሚያ ነዋሪ ሆኑት ወ/ሮ ኢፍቱ ሱፍያን ቀደም ባሉት ዓመታት ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ባገኙት የግብርና ቴክኖሎጂዎች ኑሯቸው መለወጡን ገለጸው አሁን ደግሞ የተሻሻለውን ምርጥ የዶሮ ዝርያ በማግኘታቸው ደስተኛ መሆናቸውንና ለውጥ አገኛለሁ ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

ሌላኛዋ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ጣቢያ ኤፍ ኤም 91.5 ያነጋገራቸው ወ/ሮ ሳፊያ አብዶ በበኩላቸው አንድ ተቋም አቅዶ የሰውን ኑሮ ለመቀየር አዲስ ነገር ቤትህ ድረስ ይዞ ሲመጣ ምን ያህል ደስታና መነሳሳት እንደሚፈጠርብህ ለመገመት አያስቸግርም ብለው ከዚህ ቀደም በኮምቦልቻ ወረዳ ሰርከማ በተባለ ቀበሌ አንዲት ነዋሪ ያላት ምርት በሙሉ በአንበጣ ወድሞባት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሰጣት አስራ ሁለት የተሻሻሉ ዶሮዎች በየእለቱ በሚጥሉት እንቁላል ሽያጭ ልጆቿን ለመመገብ አማራጭ የገቢ ምንጭ እንደሆነላት በሐ.ዩ. ኤፍ ኤም 91.5 ስሰማ ይህን የዶሮ ዝርያ እንዴት ማግኘት እንዳለብኝ ሳስብ ነበር ብላለች።

ስመኘው የነበረውን የዶሮ ዝርያ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የዶሮ እርባታ ትምህርትን ጨምሮ ሰፈራችን ድረስ መጥተው ስለሰጡን በአጭር ጊዜ ውስጥ ውጤታማ ለመሆን ሰርተን ኑሯችንን ለመደጎም ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ላደረገላቸውም ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል ሲል ሲሳይ ዋቄ ዘግቧል።

ሚያዚያ 28/2014 ዓ.ም