እንደ ሀገር እስካሁን ከተለቀቁት የቦሎቄ ዝርያዎች 16 ከመቶው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑና ዩኒቨርሲቲው ዝርያዎችን በማውጣት በሀገር አቀፍ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡

የብሔራዊ ዘር አጽዳቂ ቴክኒካል ኮሚቴና የብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ አባል ዶክተር ሚሊዮን እሸቴ ለሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ ሬዲዮ ኤፍ ኤም 91.5 እንደገለጹት የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ከ5 ዓመት በላይ በተለያዩ ሰባት ቦታዎች ላይ ምርመር ሲያደርግበት የቆየውን ቦሎቄ ሚኦፍቱ /DAB410/ የሚል ስም የተሰጠው ዝርያ የሁሉም ክልሎች ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ፣ የምርመር ማዕከላት ፣ ዩኒቨርሲቲዎችና አስራ አንዱ የብሔራዊ  ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ አባላት ውጤቱን ገምግመውት ውጤታማነቱን ካረጋገጡ በኋላ ጸድቆ መለቀቁን አብስረዋል።

የዝርያ ለቀቃ ጥበቃና የዘር ጥራት ቁጥጥር ተወካይ ዳይሬክተር እና የብሔራዊ ዝርያ አጽዳቂ ኮሚቴ ጸሀፊ  የሆኑት አቶ ፍሰሃ ተሾመ እንደገለጹት የሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ ያቀረበው ዝርያ በተለያዩ የዩኒቨርሲቲው ምርምር ማዕከላትና በአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ተሞክሮ ከሌሎች በተሻለ መልኩ በምርት ብዛት ፣ በንጥረ ነገር ይዘት ፣ በቀለም ፣ በቁመት በፍሬውና በውጪ ገበያ ላይ ባለው ተፈላጊነት ፣ በሽታንና ድርቅን በመቋቋም እንዲሁም ቶሎ መድረሱን የዝርያ አዳቃይን ጨምሮ አምስት ባለሙያዎችና አርሶአደሮች ገምግመው የተሻለ መሆኑ በመረጋገጣቸው ዝርያው እንዲለቀቅ ተወስኗል ብለዋል ፡፡

በሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቦሎቄ ምርመር ቡድን መሪ የሆኑት አቶ ኢብሳ አሊዪ በበኩላቸው አሁን የተለቀቀው ሚኦፍቱ የተሰኘው ዝርያ ለሐረርጌም ሆነ ለሀገሪቱ አርሶ አደሮች አማራጭና ትልቅ ዕድል መሆኑን ገልጸው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እስካሁን አስራሁለት የተለያዩ የተሻሻሉ የቦሎቄ ዝርያዎችን መልቀቁንና ለዚህም ስኬት የዩኒቨርሲቲው የቀድሞና የአሁኖቹ አመራሮች ፣ የቴክኒክና የመስክ ሰራተኞች እንዲሁም የቀድሞና የአሁኖቹ የቦሎቄ ምርምር ቡድን አባለት ምስጋና ይገባቸዋል ብለዋል። አቶ ኢብሳ አያይዘውም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ይህን አዲስ የተለቀቀ  የቦሎቄ ዝርያ ለተጠቃሚው አርሶ አደር ለማድረስ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በሐረማያ  ዩኒቨርሲቲ  የቦሎቄ ምርመር ቡድን አባልና የዶክትሬት (ሶስተኛ) ተማሪ የሆኑት አቶ ዮናስ ሞገስ ሲናገሩ በሀገር ደረጃ ከብሔራዊ ምርመር ማዕከል ቀጥሎ በሃገሪቱ ከተለቀቁት የቦሎቄ ዝርያዎች 16 በመቶ ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መሆኑና እስካሁን ከዩኒቨርሲቲዎችም ሆነ ከክልሎች ምርመር ማዕከላት ጋር ሲነጻጸር እስካሁን የደረሰበት የለም ብለዋል። አሁን ያወጡት አዲስ ዝርያ በቅርብ ከተለቀቁት የሚሻለው በያዘው የብረትና ዚንክ ንጥረ ነገርን ከሌሎቹ በተሻለ በመያዙ ብቻ ሳይሆን በውጪ ገበያም ተፈላጊ በመሆኑ ነው ብለዋል ፡፡

የመስክ ከፍተኛ ቴክኒሻን የሆኑት አቶ ብርሀኑ አስፋው ምርምሩ በባቢሌ ፣ ፈዲስ ፣ ሂርና ፣ ሐረማያ ዋናው ግቢ የምርመር ማዕከላትና የአርሶ ኣደሮች ማሳ ላይ የተካሄ መሆኑን ጠቁመው በነዚህ ቦታዎች በሙሉ ከሌሎች የቦሎቄ ዝርያዎች መካከል ሚኦፍቱ በአርሶ አደሮች ተመራጭ መሆን መቻሉን ተናግረዋል ሲል ሲሳይ ዋቄ ዘግቧል።