ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ጀነራል ሆስፒታል ሊገነባ ነው

በምስራቅ ሐረርጌ ዞን ኮምቦልቻ ወረዳ ከ300 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ በትውልደ ኢትዮጵያዊያን ዳያስፖራዎች የሚገነባ መልቲ ጀነራል ሆስፒታል የመሰረት ድንጋይ ትናንት ተቀመጠ።

ሮጀክቱ በ1 ነጥብ 6 ሄክታር መሬት ላይ የሚያርፍ ሲሆን ወጪው ሙሉ በሙሉ በውጭ ሀገራት በሚኖሩ የዞኑ ተወላጆችና በአሁኑ ግዜ አሜሪካ በሚኖሩ ትውልደ ኢትዮጵያዊያን የሚሸፈን ነው።

በወረዳው ለሚገነባው ሆስፒታል የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ፣ የኮምቦልቻ ወረዳ አስተዳደር አልዪ ኢብራሂም እና የዲያስፖራ ተወካይ ፈረሃን አህመድ የመሰረት ድንጋዩን አስቀምጠዋል።

በእለቱ ንግግር ያደረጉት የዲያስፖራ ተወካይ ፈርሀን አህመድ ማኅበረሰቡ የተሟላ ጤና አገልግሎት ለማግኘት የሚደርስበትን እንግልት ከግምት በማስገባት ሆስፒታሉን ለመገንባት መነሳሳታቸውን ገልፀዋል።

የማህበረሰቡን ፍላጎት ከግምት ውስጥ በማስገባት ሁሉም እንደየችሎታው ባለሃብቶች በገንዘባቸው ሌሎችም በጉልበታቸውና በሃሳብም ጭምር ድጋፍ የሚያደርጉ ከሆነ ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እንደሚቻል ይቻላል ብለዋል። አቶ ፈርሃን ይአያይዘውም ዲያስፖራው ወገኑን ለመርዳት በአሁኑ ወቅት ቁርጠኛ አቋም መያዙን አመልክተዋል።

የሆስፒታሉ ግንባታ ሲጠናቀቅ የጤና አገልግሎት አሰጣጥን ከመደገፍ ባሻገር ለአካባቢው ወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ትልቅ ፋያዳ እንዳለው ተገልጿል።

ውጪ የሚኖሩ ትውልድ ኢትዮጵያዊን ምቹ ሁኔታ ከተፈጠረላቸውና በአንድነት የመስራት ሁኔታ ካለ የተለያዩ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት በተለይ በትምህርትና በጤና ላይ ለመስራት ፍላጎት እንዳላቸው አቶ ፈርሃን ተናግረዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ጀማል ዩሱፍ ሆስፒታሉ በርካታ ከፍተኛ ህክምና ለሚፈልጉ ህሙማን አገልግሎት የሚሰጥበት እንደሆነ ገልፀዋል።

ሐረር ከተማ የሚገኘው የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የህይወት ፋና ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል 6 ሚሊየን የሚደርስ ተጠቃሚ የሚያገለግል መሆኑን ገልፀው የኮምቦልቻ ሆስፒታል መገንባቱ ጫናውን ይቀንሳል ብለዋል።

የሰው ልጅ ጤና ካለው ብቻ በሀገሪቷ ልማትና እድገት ላይ የሚሳተፍ በመሆኑ ይህን ለማሳካት ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ለፕሮጀክቱ ግንባታ ስኬት ከዲዛይን ጀምሮ አስፈላጊውን የሙያ ድጋፍና ትብብር እንደሚያደርግ ዶክተር ጀማል የመሰረተ ድንጋይ ሲያስቀምጡ ቃል ገብተዋል።

በሌላ በኩል የወረዳው የመንግስት አካላትና ማህበረሰቡ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።

የኮምቦልቻ ወረዳ አስተዳዳሪ አሊዪ አብራሂም በበኩላቸው ዲያስፖራው “ለሀገሬ ምን አረኩኝ” በሚል ስሜት በመነሳሳት የወገኑን ችግር ለመቅረፍ ሆስፒተሉን ለመገንባት ወደ ሥራ በመግባታቸው አመስግነዋል።

በመሆኑም ፕሮጀክቱ ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ የማኅበረሰቡ ርብርብ አስፈላጊ በመሆኑ ማኅበረሰቡ የበኩሉን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

በወረዳ የሚገኙ ነዋሪዎች በወረዳው በአይነቱ ለየት ያለ ሆስፒታል ለመገንባት መሰረት ድንጋይ በመቀመጡ ደስተኛ መሆናቸውንና ፕሮጀክቱ በግዜ እንዲጠናቀቅ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንደሚያደርጉ አሰተያየታቸውን ሰጥተዋል።

አዲስ የሚገባው ጠቅላላ ሆስፒታል 1600 ሥኴር ሜትር ላይ የሚያርፈው የሆስፒታሉ ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚገመት ዶ/ር ጀማል ዩሱፍ ተናግረዋል።

ዘጋቢ፦ ሽመልስ በቀለ
ፎቶግራፈር፦ ፉአድ አህመድ
ግንቦት 08/2014

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*