ሐረማያ ዩኒቨርሰቲ ሀረር ከተማ ለሚገኘው የአብርሃ ባሃታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ድርጅት ዊልቸርና ለአካል ድጋፍ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶች ድጋፍ አደረገ።

ሐረማያ ዩኒቨርሰቲ ለአብርሃ ባሃታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ድርጅት ግምቱ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ዊልቸርና ሌሎች ለአካል ድጋፍ የሚያገለግሉ ቁሳቁሶችን ነው ድጋፍ ያደረገው።

ዩኒቨርሲቲው ክርስቲያን ሪሊፍ ሰርቪስስ ከተሰኘ የአሜሪካ መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ጋር በመነጋጋር ያገኘውን ድጋፍ ነው ለድርጅቱ ያስረከበው።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ተወካይ ፕሮፌሰር ጄይላን ወልዪ የትምህርት ተቋሙ ማህበረሰብ ተኮር ስራዎችን ትኩረት አድርጎ እየሰራ እንደሚገኝና ወደፊትም ለተቸገሩ ወገኖች የሚያደርገውን ድጋፍ እንደሚቀጥል ገልጸዋል።

በማዕከሉ ውስጥ የሚገኙ አረጋውያን ሀገራቸውን በተለያየ ዘርፍ ሲያገለግሉ የነበሩና በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ማዕከሉ የተቀላቀሉ በመሆኑ ለሀገራቸው ቀደም ሲል ስላደረጉት ጥረት እነዚህን አረጋውያን የመንከባከብ ግዴታ ሁላችንም አለብን ብለዋል።

ወይዘሮ ምስራቅ እሸቴ የሐረሪ ክልል ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ በድጋፉ ወቅት እንደገለፁት በማዕከሉ ውስጥ ላሉ አረጋውያን ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ላደረገው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበው ዩኒቨርሲቲው በህክምናና በሌሎች ዘርፎችም ድጋፍ እንዲያደርግላቸው ጠይቀዋል።

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎትና ኢንተርፕራይዝ ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ይስሀቅ ዩሱፍ በማዕከሉ ውስጥ ለሚገኙ አረጋውያን የጤና አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎችን በመመደብ አስፈላጊው የህክምናና የጤና ድጋፎችን እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል።

የአብርሃ ባሃታ አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ተሃድሶ ድርጅት በትውልደ ኤርትራዊው አብርሃ ባሃታ በ1958 ዓ.ም የተቋቋመ ነው።

Leave a Comment

Your email address will not be published. Required fields are marked *

*