የሐረማያ ዩኒቨርስቲ አስተዳደር ቦርድ ነሐሴ 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ባካሄደው ስብሰባ የዩኒቨርስቲው ሴኔት ገምግሞ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት ለዶ/ር መንግስቱ ኡርጌ ለታ በእንስሳት ሥነ-ምግብና ሥነ-አካል ዘርፍ የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ሰጠ፡፡

ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ ለታ በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ሰሜን ሸዋ በአንጎለላና ጠራ ወረዳ ሸኖ እና ደብረብርሃን መሃከል በምትገኝ ጨኪ በምትባል ትንሽ ከተማ ሐምሌ 25 ቀን 1960 ዓ.ም. ከአባታቸው ከአቶ ኡርጌ ለታ ኩሣ እና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጥሩነሽ ቡሹ ነገዎ ተወለዱ፡፡ እድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስም የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨኪ አንደኛ ደረጃ ት/ቤት፤ የመለስተኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በሸኖ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡ ከዚያም ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ በወቅቱ አለማያ ዩኒቨርስቲ ተብሎ ይጠራ የነበረውና የአሁኑ ሐረማያ ዩኒቨርስቲ በ1978 ዓ.ም. ገብተው በእንስሳት ሣይንስና ቴክኖሎጂ ዲፕሎማ በ1980 ዓ.ም. ተመርቀዋል፡፡

ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ ከ1981 እስከ 1982 ዓ.ም. ድረስ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ በቴክኒክ ረዳትነት ደረጃ ካገለገሉ በኋላ ሥራቸውን በመልቀቅ ትምህርታቸውን በሐረማያ ዩኒቨርስቲ የቀጠሉ ሲሆን በነሐሴ 21/1985 ዓ.ም. በእንስሳት ሣይንስ በቢ.ኤስ.ሲ. ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡ ከዚያም በ1991 ዓ.ም. በእንስሳት እርባታ የኤም.ኤስ.ሲ ዲግሪያቸውን ከሐረማያ ዩኒቨርስቲ ተቀብለዋል፡፡ እንዲሁም ከሚያዝያ 1995 ዓ.ም. እስከ ሚያዝያ 1999 ዓ.ም. ድረስ ስዊድን ሀገር በሚገኘው ሲዊዲን የእርሻ ዩኒቨርስቲ ትምህርታቸውን በመከታተል የፍልስፍና ዶክትሬት ዲግሪያቸውን በእንስሳትሥነ-አካል (Animal Physiology) አግኝተዋል፡፡

ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ ከ30 ዓመታት በላይ በሐረማያ ዩኒቨርስቲ ባገለገሉበት ጊዜያት የተለያዩ የቅድመና-ድህረ-ምረቃ ትምህርቶችን አስተምረዋል፡፡ በዩኒቨርስቲው ውስጥ በማስተማር፣ በምርምርና በማህበራዊ ተሳትፎ ላበረከቱት አስተዋፅኦም የተባባሪ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ አግኝተዋል፡፡ ዶ/ር መንግስቱ ኡርጌ በዚህ ቆይታቸው ጊዜ 160 የማስትሬትና 20 የዶክተሬት ተማሪዎችን በሚገባ በማማከር ዲግሪያቸውን እጅግ በጣም ጥሩ በሆነ ሁኔታ እንዲያገኙ አስችለዋል፡፡ በሐረማያ ዩኒቨርስቲና በሌሎች ኢትዮጵያ ውስጥ በሚገኙ ዩኒቨርስቲዎችም አማካሪና የውጭ ፈታኝ በመሆኑ ብዙ ተማሪዎችን አገልግለዋል፡፡

ከማስተማርና የማማከር ሥራ በተጨማሪ ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ በግላቸውና ከተማሪዎቻቸው ጋር ካደረጓቸው የምርምር ሥራዎች ውስጥ እስከ አሁን 147 ሀገራዊና አለም አቀፋዊ ፋይዳ ያላቸው ሣይንሳዊ ፅሁፎችን በዓለም አቀፍ የምርምር ጆርናሎች ላይ አሳትመዋል፡፡ እንዲሁም ለተለያዩ ጆርናሎች በሃያሲነት / በገምጋሚነት ሰርተዋል፡፡ ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ በርካታ የምርምር ፈንዶችን ወደ ዩኒቨርስቲው ያመጡ ሲሆን ከነዚህም ውስጥ ለአካባቢው ማህበረሰብ ፋይዳ የነበራቸው እንደ ‘የተሻሻሉ ፍየሎች አረባብና ሥርጭት’ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡

ከማስተማርና ማማከር በተጨማሪ ዶ/ር መንግሥቱ ኡርጌ የእንስሳት ሣይንስ ትምህርት ክፍል ሃላፊ ፣ የምርምር ዳይሬክተር ፣ የድህረ-ምረቃ ፕሮግራም ዳይሬክተር በመሆን ዩኒቨርስቲውን አገልግለዋል፡፡