የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ለታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ለሁለተኛ ጊዜ ለመለገስ ቃል ገቡ ።
መምሀራኑና የአስተዳደር ሰራተኞቹ ለግድቡ ግንባታ የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከፍለው በማጠናቀቃቸው የቦንድ የምስክር ወረቀት ተረክበዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ባደረጉት ስብሰባ ላይ ለታላቁ የኢትዮዽያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚውል የአንድ ወር ደሞዛቸውን ከ13 ሚሊየን ብር በላይ ለሁለተኛ ጊዜ ለመለገስ ተስማምተዋል።

የዩኒቨርሲቲው የስራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢና የኦሮሚያ ክልል ምክትል ርእሰ መስተዳደር አቶ አብዱላዚዝ መሐመድ ለሰራተኞቹ የቦንድ ሰነዱን ከሰጡ በኋላ እንደገለጹት መምህራኑና የአስተዳደር ሰራተኞቹ ለህዳሴው ግድብ ዕውን መሆን የሚያደርጉት አስተዋጽኦ አበረታታች ነው።
የሕዳሴው ግድብ ሀሳብ አፍለቂና መሀንዲስ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ማንም ያልደፈረውን የአባይን ወንዝ በራስ አቅም ለመገደብ የመሰረት ድንጋይ ካስቀመጡ ወቅት ጀምሮ ሁሉም የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የቦንድ ግዥ በመፈፀም አለኝታነቱን እያሳየ ይገኛል ብለዋል።
የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዜዳንት ዶክተር ግርማ አመንቴ ለግድቡ ግንባታ የዩኒቨርሲቲው ሁለት ሺህ 740 መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች በመጀመሪያው ዙር ከአራት ሚሊየን ብር በላይ የቦንድ ግዠ መፈጸማቸውን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የተቋሙ መምህራንና የአስተዳደር ሰራተኞች ቁጥር ከአምስት ሺህ በላይ መድረሱን አስታውሰው በሁለተኛ ዙር ከ13 ሚሊየን ብር የሚበልጥ የቦንድ ግዥ እንደሚፈጸ ተናግረዋል።
በቦንድ አሰጣጥ ፕሮግራሙ ላይ ከተሳተፉት መካከል መምህር ፈየራ ዲንሳና የአስተዳደር ሰራተኛ የሆኑት አቶ ከማል ኡመር በሰጡት አስተያየት የህዳሴ ግድብ ከዳር እስኪደርስ የወር ደሞዛቸውን ከመስጠት እንደማይቆጠቡ አረጋግጠዋል።
የግድቡ ስራ መፋጠን ለሚያደርጉት ድጋፍ መነሳሳትን እየፈጠረላቸው መሆኑንም አስታውቀዋል።