በሸምሰዲን መሀመድ/ከሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ህዝብና አለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት

የፊታችን ህዳር 29 ቀን 2007 ዓ.ም በሀገር አቀፍ ደረጃ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በደማቅ ሁኔታ የሚከበረውን የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በዓልን ምክንያት በማድረግ በዩኒቨርሲቲያን ዋናው ግቢ የሚገኙ ተማሪዎች አካባቢያቸውን ከማጽዳት ጎንለጎን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ የደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ በዘመቻ ወጥተው በልማት ስራ ላይ ማክበር ጀምረዋል፡፡

ህዳር 20 ቀን 2007 ዓ.ም ለግማሽ ቀን በተካሄደው በዚሁ የጽዳትና የበቆሎ መሸልቀቅ ስራ ላይ የተሳተፉት ከተለያዩ ክበባት የተውጣጡ ተማሪዎች ሲሆኑ በእለቱ በሰጡት አስተያየት በዓሉ አንድነታቸውን ከማጠናከር ባሻገር መከባበርንና መቻቻልን እንደሚፈጥርላቸው ብሎም ሀገራችን እያከናወነች ያለውን ልማታዊ ጉዞ ከግብ ለማድረስ ታላቅ ጠቀሜታ እንዳው ገልጸዋል፡፡ የልማቱም ግንባር ቀደም ተዋናይ በመሆን የበኩላቸውን ለመዋጣት ከመቼውም በላይ ዝግጁነታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘደንት ዶ/ር ግርማ አመንቴ በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት በዓሉ በዩነቨርሲቲው ውስጥ መከባበሩ የሚሰጠው ፋይዳ ትልቅ መሆኑን ገልጸው አገራችን የጀመረችውን የልማት መስመር ከግብ ለማድረስ ብሎም ዋና ጠላትችን የሆነውን ድህነት ለማሸነፍ አንድነታችን ውበታችን መሆኑን አውቀን በጋራ ለስራ መነሳት አለብን ብለዋል፡፡

ዶ/ር ግርማ አክለውም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በሀገሪቱ እየተካደ ያለው የዲሞክራሲ ስርዓት ይበልጥ እንዲጎለብት ብሎም የተጀመሩት የልማት ሥራዎች ቀጣይነት እንዲኖራቸው የሚጫወቱት ሚና ከፍተኛ መሆኑን ጠቅሰው ዩኒቨርሲቲዎች ማለት ትንሽዋን ኢትዮጵያ የሚወክሉ እንደመሆናቸው መጠን ይህ የምናከብረው የብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ቀን በህገ መንግስቱ የተገኙትን ውጤቶች በማጠናከር በህዝቦች መካከል የለውን የቆየ ወንድማማችነት ትስስርን እንደሚያጠናክር ያላቸውን እምነት አስረድተዋል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ውስጥ በህግ መንግስታችን የደመቀ ኢትዮጵያዊነታችን ለህዳሲያችን በሚል መሪ ሃሳብ መከበር የጀመረው ይህ በዓል ለአንድ ሳምንት በተለያዩ ክንዋኔዎች የሚቆይ ሲሆን በህገ መንግስቱና በፌዴራል ስርዓቱ ዙሪያ የጥያቄና መልስ ውድድር እንዲሁም ተማሪዎችና ሰራተኞች የሚሳፉበት የፓናል ውይይት አርብ ህዳር 26 ቀን 2007 ዓ.ም እንደሚደረግ ከበዓሉ የድርጊት መርሀግብር ለማወቅ ተችሏል፡፡