የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት በመልካም ስነ ምግባር በመታነጽ ማህበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ተገለጸ።

  በስልጠናው መክፈቻ ላይ የተገኙት የተማሪዎች ጉዳይና የአስተዳደር ምክትል ፕሬዝዳንት ዶክተር ፍቃዱ በየነ ባደረጉት ንግግር እንደገለጹት የስነ ምግባር ችግር የአንድ ሀገርን ኢኮኖሚና ማህበራዊ የእድገት ጉዞን በከፍተኛ ሁኔታ ይጎዳል።

ይህንንም ለመከላከል ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው በቀለም ትምህርት ብቻ እውቀት ቀስመው የሚሄዱበት ሳይሆን በስነ ምግባርም ታንጸው መውጣት ይኖርባቸዋል።

 በዚህም ዩኒቨርሲቲው ከ1998 ጀምሮ ለእጩ ተመራቂ ተማሪዎች ከመመረቃቸው በፊት የስነ ምግባር፣የመልካም አስተዳደርና ጸረ ሙስና ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና እየሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

 ይህም ተማሪዎች ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት የሚያጋጥሟቸውን የስነ ምግባር ችግር በአጭሩ እንዲቀረፍ ከማድረጉ በተጨማሪ ለማህበረሰቡ የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ማስቻሉን ተናግረዋል።

 እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ትምህርታቸውን አጠናቀው ወደ ስራ በሚሰማሩበት ወቅት በመልካም ስነ ምግባር ማህበረሰቡን በቅንነትና በታማኝነት ማገልገል እንደሚጠበቅባቸው ዶክተር ፍቃዱ አስገንዝበዋል።

 የዩኒቨርሲው የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና  ጽህፈት ቤት ሃላፊ መምህር ትግሉ መለሰ በበኩላቸው ለአንድ ሀገር የልማት እድገት በእውቀት የበለጸገ ዜጋ ማፍራት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው።

 ተማሪዎች በተቋማቸው ቆይታ ከቀለም ትምህርት ጎን ለጎን በስነ ምግባር የጠለቀ  እውቀት ይዘው መሄዳቸው ማህበረሰቡን በቅንነት፣በታማኝነትና እንዲያገለግሉ ያስችላል።

 እንዲሁም ሃላፊነትን ባግባቡ እንዲጠቀሙ የመንግስት ንብረትን በአግባቡ እንዲያስተዳድሩና ለሚያጋጥማቸውና ለሚጠየቁት ማንኛውም ጥያቄ ተገቢ ምላሽ ለመስጠት ስልጠናው እንደሚያስችል አስረድተዋል።

 የዩኒቨርሲቲው የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ጽህፈት ቤትና የተማሪዎች ክበብ በጋራ ባዘጋጁት የአምስት ቀናት ስልጠና 4 ሺህ የሚጠጉ እጩ ተመራቂ ተማሪዎች ከፌዴራል የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን በመጡ ባለሞያዎች ስልጠና  እንደወሰዱ መምህር ትግሉ አክለው ገልጸዋል።