ዶ/ር አስፋው ከበደ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ዲን ንግግር

 

የሐረማያ ዩኒቨርሲቲና ህንድ አገር ከሚገኝ ቢ ኤም ቪ ኤስ ኤስ ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር በምስራቅ ኢትዮጵያ አጎራባች ክልሎች ለሚገኙ 300 አካል ጉዳተኞች የሰው ሰራሽ እግር ተከላና የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የመሰረት ልማት ማስፋፊያ ፕሮጀክት ምረቃ ላይ የተደረገ ንግግር

ክቡር ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ – የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ኘሬዚዳንት
የተከበራችሁ የፌዴራልና የክልል መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፡-
የተከበራችሁ የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ የአስተዳደር ቦርድ አባላት፡-
ጥሪ የተደረገላችሁ እንግዶች፡-
ክቡራትና ክቡራን፡-

በቅድሚያ ጥሪያችንን አክብራችሁ ወደ አንጋፋው ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ እንኳን በደህና መጣችሁ ማለት እፈልጋለሁ፡፡
የማህበረሰብ አገልግሎትና ልማት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ካሉአቸው ሶስት ትላልቅ ተልዕኮዎች አንዱ ነው፡፡ ሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ይህንን ተልዕኮ በላቀ ለመፈፀም የተሻለ አደረጃጀት በመዘርጋትና የማህበረሰብ አገልግሎትና ልማት ፎኖተ-ካርታ በአሳታፊነት በማዘጋጀት ሰፊ የሥራ እንቅስቃሴ እያደረገ ይገኛል፡፡ በፍኖተ-ካርታው መሠረት በተጨባጭ በየዓመቱ በተለያዩ ርዕሰ-ጉዳዮች፡- በትምህርት፣ በጤና፣ በሥራ ፈጠራና በመሳሰሉት የአቅም ግንባታ ስልጠና ይሰጣል፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የግብርናና የተፈጥሮ ሀብት አያያዝ ቴክኖሎጂን ያሸጋግራል፤ ያላምዳል፤ በአካባቢው ላሉት ት/ቤቶችና የጤና ተቋማት የቁሳቁስና የተለያዩ ድጋፎችን ያደርጋል፤ በሕይወት ፋና ሆስፒታል የሕክምና አገልግሎት ይሰጣል፤ የተቀናጀ የሐረማያ ተፋሰስ ልማት ያከናውናል፤ በምሥራቅ ኢትዮጵያ በ43 ማዕከላት ነፃ የሕግ አገልግሎት ይሰጣል፤ የመሠረተ-ልማት ሥራዎች፡- መንገድ፣ የመጠጥ ውሃ፣ የሥራ ቦታዎችንና የመሳሰሉትን እየሰራ ይገኛል፡፡ በቀጣይነትም በዙሪያችን ላሉት ማህበረሰብና ተቋማት ቅድሚያና ልዩ ትኩረት በመስጠት የማህበረሰብ አገልግሎትና ልማት ሥራዎቻችንን አጠናክረን ለመቀጠል አቅደን እየሠራን እንገኛለን፡፡

ክቡር ኘሬዚዳንት፡-
ክቡራትና ክቡራን፡-
ትምህርትን ለሁሉም ዜጐች ተደራሽና የተመቻቸ ለማድረግ እየተደረገ ያለውን ሁለገብ ጥረት ለማሳካት በዩኒቨርሲቲያችን ላሉ 96 አካል ጉዳተኛ ተማሪዎች

ሁኔታዎችን የተመቻቸ ለማድረግ ምቹ የመማሪያ ክፍሎች፣ የመኖሪያ ቤቶች፣ የማንበቢያ ክፍሎች፣ የመፀዳጃ ቤቶች፣ መንገዶችና ቁሳቁሶችን በማሟላት ትምህርታቸውን በአግባቡ እንዲከታተሉ እያደረግን እንገኛለን፡፡ የተለያዩ የትምህርት ድጋፍ፣ የቁሳቁስና በነፍስ ወከፍ በየወሩ ከብር 200 በላይ የፋይናንስ ድጋፎችን እናደርጋለን፡፡ ተመሳሳይ ድጋፎችን ዩኒቨርሲቲያችን አካባቢው ለሚገኙ ሌሎች አካል ጉዳተኞች ተደራሽ ለማድረግ ህንድ አገር ከሚገኘው ቢ.ኤም.ቪ.ኤስ. ግብረ-ሰናይ ድርጅት ጋር በፈጠርነው ግኑኝነት፣ ማመቻቸትና ድጋፍ ከምሥራቅ ኢትዮጵያ እስከ 300 የአካል ጉዳተኞች ሰው ሰራሽ እግር እንዲሰራላቸው ለማድረግ ተችሏል፡፡ ለዚህ የተቀደሰ ሰብአዊ በጐ ሥራ ቢ.ኤም.ቪ.ኤስ. ድርጅትን፣ እርዳታው እንዲሳካ ያደረጉትን ድርጅቶችን፣ የሕንድ ኤምባሲንና በተለያዩ ጉዳዮች የተባበሩንን ሁሉ በራሴ፣ በሐረማያ ዩኒቨርሲቲና በተጠቃሚዎች ስም በጣም አመሰግናለሁ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ዩኒቨርሲቲያችን ከሕንድ የከፍተኛ ትምህርትና ምርምር ተቋማት ጋር አጋርነት ለመመስረትና ለማጠናከር ፍላጐቱ መሆኑን እገልፃለሁ፡፡
የአገራችንን የ70 በመቶ ሳይንስና ቴክኖሎጂና የ30 በመቶ የህብረተሰብ ሳይንስ የከፍተኛ ትምህርት ፖሊሲ በተገቢው ለማሳካትና የትምህርት ጥራትን ለማጐልበት ዩኒቨርሲቲያችን የቴክኖሎጂ ተቋም መሠረተ ልማት ማስፋፊያ አከናውኗል፡፡ ማስፋፍያውም የመማሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎች፣ ዎርክሾፖች፣ የተማሪዎች መኖሪያ ሕንፃዎችንና መንገዶችን ያካተተ ነው፡፡ የዩኒቨርሲቲያችን የቴክኖሎጂ ተቋም 10 የቅድመ-ምረቃ የምህንድስና የስልጠና መስኮች፣ 9 የድህረ-ምረቃ የምህንድስና የስልጠና መስኮችን ትምህርት በማስተማር 40 በመቶ የዩኒቨርሲቲውን መደበኛ ተማሪዎችን እያገለገለ የሚገኝ ተቋም ነው፡፡ የተገነባው መሠረተ ልማት የዩኒቨርሲቲያችን የቴክኖሎጂ ትምህርት የበለጠ ተግባር ተኮር እንዲሆንና ለመማር-ማስተማር የተመቻቸና የተሳለጠ እንዲሆን ያደርጋል፡፡ ተቋሙንም የሐረማያ ቴክኖሎጂ ተቋም ተብሎ እንዲሰየም ዩኒቨርሲቲው ወስኖአል፡፡ ይህም መሠረተ-ልማት ማስፋፍያ በተጓዳኝ ዛሬ ስለሚመረቅ ክቡራን እንግዶች እንድትመርቁልንና ተቋሙን እንድትጐበኙ በትህትና እጠይቃለሁ፡፡
በድጋሜ እንኳን ደህና መጣችሁ !
አመሰግናለሁ !

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.