ዩኒቨርሲቲው በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቲማቲም ዝርያዎችን እያስተዋወቀ ነው

 

a

ሀረር ሚያዚያ 25/2009 የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ ድርቅንና በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ የቲማቲም ዝርያዎችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑን ገለፀ።
የዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ልማት ምክትል ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ከበደ ወልደ ጻዲቅ ለኢዜአ እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲው ለአካባቢው አርሶ አደሮች እያስተዋወቀ የሚገኘው ከአሜሪካ፣ ቻይና፣ ህንድ፣ እስራኤልና አውስትራሊያ ያስመጣቸውን አራት የቲማቲም ዝርያዎች ነው። ዩኒቨርሲቲው በምርምር ጣቢያ ለሁለት ዓመታት ባደረገው የዝርያ ማላመድ ለአካባቢው የአየር ሁኔታ ተስማሚ መሆናቸው መረጋገጡንም ተናግረዋል ። በተጨማሪም በሐረማያ ወረዳ፣ በድሬዳዋ አስተዳደርና በሐረሪ ክልል በ610 አርሶ አደሮች ማሳ ዝርያዎቹን የማለማመድና የማስተዋወቅ ስራ እየተካሄደ መሆኑን ጠቁመዋል ።
እንደ ፕሬዝዳንቱ ገለፃ የቲማቲም ዝርያዎቹ በአርሶ አደሩ ማሳ በሄክታር እስከ 500 ኩንታል ምርት እንደሚሰጡ ተረጋግጧል ። “በዚህም ከነባሩ ዝርያ ከሚገኘው 100 ኩንታል አብላጫ ምርት የሚሰጡ
በመሆናቸው በአካባቢው አርሶ አደሮችና የግብርና ቢሮዎች ተቀባይነት አግኝተዋል ” ብለዋል ። ዩኒቨርሲቲው ከአጋር አካላትና ከዘር አቅራቢ ድርጅቶች ጋር በመሆን በቀጣይ በሽንኩርትና ቃርያ ዝርያዎች ላይ የማላመድና የማስፋፋት ስራ ለመካሄድ በዝግጅት ላይ መሆኑን ፕሮፌሰር ከበደ አስታውቀዋል ። በድሬዳዋ ግብርና፣ ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ የግብርና ኤክስቴንሽን አብይ የስራ ሂደት መሪ አቶ መሐመድ አብዱላሂ በበኩላቸው ከሁለት አመት በፊት በሁለት ቀበሌዎች የተጀመረው የቲማቲም ዝርያ የማላመድና የማስተዋወቅ ስራ ውጤታማ መሆኑን ተናግረዋል ። የዝርያ ማላመድና ማስተዋወቅ ልማቱ 95 ነጥብ 5 ሄክታር የአርሶ አደሮች ማሳ ላይ ውሀን በቁጠባ በመጠቀም የተካሄደ መሆኑን ገልፀዋል ። እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ በልማቱ ተሳታፊ የሆኑ 540 አባወራ አርሶ አደሮች በተፈጠረላቸው የገበያ ትስስርም ተጠቃሚ ሆነዋል ። “ዝርያዎቹ በሽታና ሙቀትን የሚቋቋሙና በዓመት ከሁለት ጊዜ በላይ ሊመረቱ የሚችሉ በመሆናቸው የአርሶ አደሩን በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ ያላቸው ሆነው ተገኝተዋል ” ብለዋል አቶ መሀመድ። በሐረሪ ክልል የሐዋዩ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ከዲር ሙሳ በሰጡት አስተያየት “ቀደም ሲል የምጠቀመው የቲማቲም ዘር ፀሀይና በሽታን መቋቋም ስለማይችል
የተፈለገውን ምርት ሊሰጠኝ አልቻለም” ብለዋል። አሁን እየዘሩት ያለው “ሻንቲ” የተሰኘ የቲማቲም ዝርያ ፀሀይና በሽታን ተቋቁሞ በሶስት ወራት ጊዜ የሚደርስ መሆኑን ተናግረዋል ። በሩብ ሄክታር ማሳቸው ላይ ከዘሩት የቲማቲም ዝርያ 30 ሳጥን ምርት ማግኘታቸውን ጠቅሰዋል ። እንደ አርሶ አደሩ ገለፃ ከቲማቲም ምርት ሽያጭ ያገኙት 22 ሺህ ብር ገቢ ከዚህ ቀደም በማሳው ላይ ከሚያለሙት ጫት ከአንድ ጊዜ ሽያጭ ያገኙ ከነበረው ገቢ የተሻለ ነው ። ሌላው የሀረማያ ወረዳ ቱጂ ገቢሳ ቀበሌ አርሶ አደር መሀመድ አደም በበኩላቸው ” በአነስተኛ ማሳዬ ላይ የዘራሁት አዲሱ የቲማቲም ዝርያ ፈጥኖ የሚደርስና በመጠንና በክብደቱም ቀድሞ ከምዘራው የተሻለ ነው ” ብለዋል ። በዚህ አመት በመጀመሪያ ዙር መስኖ ከዘሩት የቲማቲም ዝርያ ከሰበሰቡት ምርት ሽያጭ 30 ሺህ ብር ገቢ በማግኘት ተጠቃሚ መሆናቸውን አርሶ አደር መሀመድ ተናግረዋል ። የሐረማያ ዩኒቨርሲቲ በሽታን ተቋቁመው ከፍተኛ ምርት የሚሰጡ 56 የቲማቲም፣ የሽንኩርትና የቃሪያ ዝርያ አይነቶችን በተለያዩ አካባቢዎች በአርሶ
አደሩ ማሳ ላይ እያላመደና እያስተዋወቀ መሆኑ ታውቋል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published.

HTML tags are not allowed.